ዜና፡ መንግስት ከታጠቁ ሀይሎች ጋር ለሰላም ንግግርና ለድርድር በር እንዲከፍትና አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲታወጅ አብን ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 17/ 2016 ዓ/ም፦ ልይነቶች በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ጥረት ማድረግ የሰለጠነና ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ አካሄድ መሆኑን በመገንዘበ መንግስት ከታጠቁ ሀይሎች ጋር ለሰላም ንግግርና ለድርድር በር እንዲከፍት እና አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲታወጅ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ጠየቀ። 

ፓርቲው በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ትላንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ የሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም የአማራ ክልል የሚገኝበት ፖለቲካዊ ቀውስና ምስቅልቅል ወደ ቀደመ ሰላም ለመመለስ የፖለቲካ ልዩነቶች ከሃቀኛ ውይይትና ድርድር በላይ አይደሉም ብሎ እንደሚያምን አስታውቋል። 

አብን እንዲካሄድ ጥሪ ባቀረበው የድርድር ሂደቱም የሀይማኖት አባቶች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሙህራንና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የተሳተፉበት፤ ተአማኒ፣ ግልፅ እና አካታች ፣ መደማመጥና በጋራ መረዳዳት ላይ የተመሰረተ፣ በውጤቱም ሁሉንም ወገኖች አትራፊ የሚያደርግና ዘላቂ ድል የሚያጎናፅፍ ፤ የህዝብን ጥቅም ከፊት ያስቀደመ የሀገርን ሰላም የሚያረጋግጥ እንዲሆን አሳስቧል። 

ድርጅቱ በመግለጫው የአማራ ህዝብ በተደጋጋሚ በሰላማዊ መንገድ ያነሳቸው ጥያቄዎች በመንግስት በኩል ተገቢውን ትኩረትና ምላሽ አለማግኘታቸው ጠቅሶ “አለፍ ሲልም በሰላማዊ መንገድ ጥያቄዎቹን ማንሳቱ እንደ ድክመት መቆጠሩ ህዝባችንን ለጦርነትና ሰፊ የሰላም ዕጦት ተጋላጭ አድርጎታል” ብሏል፡፡

ፓረቲው አክሎም “ህዝባችን ከአውዳሚ ወረራና ጦርነት ማግስት ለሰላም ሙሉ ድጋፍ ባሳየበት ወቅት በታየ የመድረክ እጦት፣ የሃይል አሰላለፍ ለውጥ የተፈጠረ የሚያስመስሉና መስመር የጣሱ የአደባባይ ላይ ግንኙነቶች መስተለዋላቸው፣ መርህአልባና ሃላፊነት የጎደላቸው የአንዳንድ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ይፋዊ ንግግሮች፣ እንዲሁም  ህዝባችን ተስፋ የጣለበት የሰላም አየር እውን ከመሆኑ ይልቅ ለሰፊ ጥርጣሬና ለሴራ ትንተና የተጋለጠበት ሁኔት በሰፊው እንዲፈጠር አድርጓል” ሲል ከሷል፡፡ 

መንግስት፣ ህዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጥ እንዲሁም በየአካባቢው በትጥቅ ትግል የተሰለፉ አካላት ህዝቡ ያለበትን ማህበራዊ ቀውሶች በመረዳት ለሰላማዊ ንግግር እና ድርድር አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጡ አብን ጥሪውን አቅርቧል፡፡

በተጨማሪም ሁሉም ተፋላሚ ሃይሎች፤ መንገዶች ክፍት እንዲሆኑ እንዲያደርጉ፤ የትምህርትና ጤና አገልግሎቶች ሳይስተጓጎሉ ለህዝብ እንዲዳረሱ ተገቢውን ሃላፊነት እንዲወጡ አሳስቧል፡፡ “በግጭቱ ወቅት ለተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካል ተጣርቶ አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ፤ የተፈናቀሉ ወገኖች እንዲመለሱ እና በተለይም በሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ለኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ የሆነውን አውራ ጎዳና አካባቢ የኦሮሚያ መንግስት የፀጥታ አካላት ፍፁም ኢ-ህገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ አካባቢውን ተቆጣጥረው በመያዝ የአካባቢውን ነዋሪ ህዝብ በማፈናቀል ለዘርፈ ብዙ ችግር የዳረጉ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲታረም” ሲል ፓርቲው ጥሪ እናስተላልፏል”፡፡

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ ቅዳሜ ዕለት በክልሉ ወቅተዊ ጉዳዮች እና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት መድረክ ላይ መንግሥት ተደጋጋሚ ውይይቶችን ማድረጉን እና ሰላማዊ አማራጮችን ማቅረቡንም ገልፀዋል። መንግሥት ሁልጊዜም ለውይይት ዝግጁ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ርእሰ መሥተዳደሩ በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም እጦት ዜጎችን ለችግር ማጋለጡን ገልፀዋል። ክልሉ በኑሮ ውድነት፣ በሥራ እድል ፈጠራ እና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ችግር ያለበት መሆኑን አመላክተዋል። አሁን ያለው የክልሉ መሪ የተወሳሰበ እና ችግር በበዛበት ሁኔታ የሚመራ መሆኑንም ነው ያስታወቁት።አስ

Exit mobile version