ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በታንዛንያ ሲካሄድ የነበረው ሁለተኛው ዙር የመንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ድርድር ያለ ውጤት መጠናቀቁን መንግስት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 11/2016 ዓ.ም፡- ባለፉት ሁለት ሳምንታት በኢትዮጵያ መንግስት እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ) መካከል በታንዛንያ ዳሬሰላም ሲካሄደ የቆየው የሰላም ድርድር ያለውጤት መጠናቀቁን መንግስት አስታወቀ። ለድርድሩ አለመሳካት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን (ሸኔ) ተጠያቂ አድርጓል።

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ማምሻውን ይዞት በወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ) በዳሬሰላሙ ድርድር ይዟቸው ይቀርባሉ ብሎ መንግስት ጠብቆ የነበረው ነጥቦች ሀገሪቱ ከደረሰችበት ምዕራፍ ጋር የተጣጣሙ ይሆናሉ የሚል እንደነበር ገልጾ ነገር ግን በዳሬሰላሙ ድርድር ቡድኑ ይዞት የቀረበው የድርድር ነጥብ “መንግሥት አዝሎ መንግሥት ያድርገኝ” የሚል አጉራ ዘለልነት ያለፈ የድርደር ነጥብ ነው ሲል ተችቷል።

መንግስት በመግለጫው የሽብር ቡድኑ ሲል የጠራው በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ) በሰላም ጊዜ እንዴት መኖር እንዳለበት ለማሰብ ቸግሮት ታይቷል ብሏል። በዜጎች ደምና እንግልት መነገዱን መርጧል ሲል ቡድኑን ኮንኗል።

የኢፌዴሪ መንግሥት ለሰላማዊ መፍትሔ ያለው አቋም እንደተጠበቀ ሆኖ ሕግና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የማስከበር ተልዕኮውን አጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል።

ውይይቱ እንዲሳካ ጥረት ሲያደርጉ ለነበሩ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርቧል።

ከወራት በፊት በታንዛንያ ዛንዚባር ውይይት ተካሂዶ እንደነበር ያወሳው የመንግስት መግለጫ በወቅቱ ስምምነት ላይ ያልተደረሰው በቡድኑ ምክንያት ነው ሲል ገልጿል።

ከአምስት አመታት በፊት በሀገሪቱ ለውጥ በመጣበት ወቅት የተመለሱ ጉዳዮችን ከማነብነብ ውጭ የሚቆጠርና የሚቋጠር አጀንዳ ማምጣት ባለመቻሉ የዛንዚባሩ ድርድር በመንግስት ይሁንታ ተቋርጦ እንዲቀጥል ተደርጓል ሲል አትቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በዛንዚባሩ ውይይት በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በኩል ከ60 ዓመታት በፊት የኦሮሞም የሌሎች የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችም ሁሉ ጥያቄዎች የነበሩና ተመልሰው ያደሩ ጥያቄዎችን አንስቷል ብሏል።

የሰላም ድርድሩ እዚህ ደረጃ እንዴት ደረሰ?


በሰላም ድርድሩ የተቀመጡት ሁለቱ ሀይሎች ባለፉት አምስት አመታት በኦሮምያ ክልል የበርካቶችን ህይወት የቀጠፈውን እና ይህ ነው የማይባል ውድመት ያስከተለውን ጦርነት በሰላም ድርድር ለመፍታት ፍላጎት እንዳላቸው ባሳለፍነው አመት ነበር። በክልሉ የተፈጠረውን ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ በወቅቱ በሀገሪቱ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሆኑ የክልሉ ተወካዮችን ጨምሮ የአሜሪካን መንግስት ጥሪ ማቅረብ ጀምረው ነበር።   

ሚያዚያ 15 ቀን 2015 ዓ.ም የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንዲያበቃ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት በተዘጋጀ የሽልማት እና የእውቅና መርሃ ግብር ላይ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ባደረጉት ንግግር መንግስት ከ“ኦነግ ሸኔ” ጋር በዛንዚባር ከሚያዚያ 17 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ድርድር እንደሚያደርጉ ማስታወቃቸውን ተከትሎ የመጀመሪያው የድርድሩ ሂደት መጀመሩ ይታወሳል።

የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ለበርካታ ግዜያት ታማኝ በሆኑ ሶሰተኛ ወገኖች ለመደራደር ዝግኙ ነኝ ሲል ይደመጥ ነበር። በሰራዊቱ ይፋ ባደረገው ማኒፌስቶ እንዳተተው በሀገሪቱ ላለው ዘርፈ ብዙ ቀውስ ብቸኛው እና ዘላቂ መፍትሄ  የሚያመጣው ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት ሲደረግ ነው ብሎ እንደሚያምን አስታወቋል።

ጠ/ሚንስትር አብይ ከኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ጋር በታንዛኒያ ድርድር እንደሚጀመር መግለፃቸውን ተከትሎ ቡድኑ ባወጣው መግለጫ መንግስት ሶስተኛ አካል ባለበት ድርድር ለማድርግ የቀረቡ ቅድመ ሁኔታዎችን በመቀበሉ ድርድሩ እንደሚጀመር ማረጋገጡ በዘገባው ተካቷል፡፡

በመንግስትና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መካከል በታንዛኒያ የተካሄደው ድርድር ሳምንት ያክል ከፈጀ በኋላ ከስምምነት ላይ መድረስ አለመቻሉን መንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በየፊናቸው ባወጡት መግለጫ ማስታወቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በወቅቱ በመንግስት በኩል የሰላም ድርድሩ የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቀቀ በሚል የተገለጸ ሲሆን ውይይቱ በአብዛኛው በአዎንታዊ መልኩ መከናወኑን በመግለጽ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ግን በዚህኛው የውይይት ምዕራፍ ስምምነት ላይ ለመድረስ አልተቻለም ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ አመላክቷል፡፡ ግጭቱን በዘላቂነትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማስቆም እንዲቻል ሁለቱም አካላት የሰላም ውይይቱን መቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ላይ ተግባብተዋል ብሏል መግለጫው።

የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በበኩሉ ባወጣው ምግለጫ የመጀመሪያው የድርድሩ ምዕራፍ መጠናቀቁን ገልፆ በወሳኝ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ላይ አለመደረሱን አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከመግባባት ላይ መደረሱን ገልጧል፡፡

ከስድስት ወራት በኋላ በፌደራል መንግስቱ እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል በታንዛንያ ዳሬሰላም ሁለተኛው ዙር የሰላም ውይይት ጥቅምት 27 ቀን 2016 ዓ.ም መጀመሩን ጉዳዩን ከሚከታተሉ ሁለት ዲፕሎማቶች በማረጋገጥ መዘገባችን ይታወሳል።

በሰላም ውይይቱ ላይ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መሪ ኩምሳ ደሪባ በቅጽል ስሙ ጃል ማሮ እና ምክትላቸው እና የደቡብ እዙ መሪ ገመቹ ረጋሳ በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ በዘገባችን ተካቷል።

የዳሬ ሰላሙ ድርድር ከመካሄዱ አስቀድሞ ለሶስት ሳምንታት የፌደራል መንግስት እና የኦሮምያ ክልል መንግስት ከፍተኛ ሃለፊዎች እንዲሁም ሁለት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አመራሮች ተሳታፊ የሆኑበት ውጤታማ የተባለ የፖለቲካ ውይይቱ መካሄዱ አዲስ ስታንዳርድ ከምንጮቻ መረዳቷን በዘገባችን ተገልጿል።

ውይይቱ ውጤታማ ስለነበር እና በዚህም ምክንያት የፌደራል መንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች የተሳተፉበት ውይይት ትላንት ጥቅምት 27 ቀን 2016 ዓ.ም መጀመሩን ምንጮቻችን ገልጸዋል።  

ከሁለቱም ወገን ከሳምንታት በፊት በተካሄደው በቀደመው የፖለቲካ ውይይት ተካፋይ የነበሩ ከፍተኛ አመራሮች ድርድሩ በስኬት ከተከናወነ ለፊርማ ስነስርአቱ ተካፋይ እንደሚሆኑ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የዲፕሎማቲክ ምንጮቻችን ጠቁመዋል።

በዳሬሰላም በመካሄድ ላይ ባለው ሁለተኛው ዙር የሰላም ውይይትን በማመቻቸት ረገድ እና በማወያየቱ ዙሪያ አሜሪካ፣ ኢጋድ፣ ኬንያ እና ኖርዌ ቁልፍ ሚና መጫወት ላይ እንደሚገኙ የአዲስ ስታንዳርድ ዲፕሎማቲክ ምንጮች አስታውቀዋል።

አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ዋና ተወካዯ ማይክ ሀመር በኩል ሚናዋን እየተጫወተች መሆኗን የጠቆሙን ምንጮች የኢጋድ ከፍተኛ ሃላፊዎች እንዲሁም የኬንያ እና ኖርዌ ተወካዮችም እንደሚገኙ አመላክተዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button