ቢዝነስዜና

ዜና፡ #የአማራ ክልል በበጀት አመቱ የአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ተኪ ምርቶችን ለማምረት ማቀዱን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28/2016 ዓ.ም፡- በ2016 በጀት አመት አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ተኪ ምርቶችን ለማምረት መታቀዱን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በአማራ ክልል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ጀምሮ በዘርፉ በርካታ ውጤቶችን ማስገኘት መቻሉን እና ከጨርቃ ጨርቅ፣ ከማኑፋክቸሪንግና ከተለያዩ የኢንዱስትሪ ዘርፎች የሚገኙ ተኪ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ገቢ ለማግኘት እንደሚሠራ የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ተፈሪ ታረቀኝ መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘገባ አመላክቷል።

በተያዘው በጀት አመት ከአምስት ሺህ በላይ ለሆኑ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ቢታቀድም በክልሉ ባጋጠመው የጸጥታ መደፍረስ ምክንያት በሩብ አመቱ የኢንቨስትመንት ፍሰት መዳከሙን ገልጸዋል ብሏል።

የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ከማህበረሰቡና ከፀጥታ አካሉ ጋር በመረባረብ በመፍታት በሩብ ዓመቱ የባከነውን ጊዜ ለማካካስና የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ በትኩረት እንደሚሠራ መናገራቸውን አካቷል።

በንቅናቄው በ2015 በጀት ዓመት በአጠቃላይ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ በተኪ ምርት በማዘጋጀት የውጭ ምንዛሬን ማዳን መቻሉን እና በ2016 በጀት ዓመት በተኪ ምርቶች አማካኝነት ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ለማዳን መታቀዱን መናገራቸውን ዘገባው አስታውቋል፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተፈሪ ታረቀኝ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አዳዲስ የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮችን መሳብ፣ የተኪ ምርቶችን ምርት ማሳደግ፣ ነባር ኢንዱስትሪዎች ላይ ያሉ ማነቆዎችን መፍታት የሚሉ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡

በ2015 በጀት ዓመት ከአምስት ሺህ 700 በላይ አዳዲስ ባለሀብቶች ወደ ክልሉ መጥተው የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን ተናግረው ያለው ዘገባው 578 ባለሀብቶች 780 ሄክታር መሬት ተቀብለው ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል ብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

28 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር የቻሉ 255 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን ወደሥራ ከማስገባት በተጨማሪም በተለያዩ ማክንያቶች ሥራ ያቆሙና የማምረት አቅማቸው ዝቅተኛ የነበሩ 149 ፕሮጀክቶች በሙሉ አቅም ወደሥራ እንዲገቡ መደረጉን ሃላፊው መግለጻቸውን ዘገባው አካቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button