ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ በኢትዮጵያ ሰብአዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ህይወት ሳይጠፋ ምላሽ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ነው ሲሉ አቶ ደመቀ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24/2016 ዓ.ም፡- የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ኢትዮጵያ በራሷ ምላሽ የመስጠት አቅም እንድትፈጥር የተቀናጀ ርብርብ እንደሚያስፈልግ የብሄራዊ አደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት አመራር ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን ትላንት ጥቅምት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደበት ወቅት ንግግር ያደረጉት የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ህይወት ሳይጠፋና የከፋ ጉዳት ሳይደርስ የተቀናጀ ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚገባ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በክልሎቹ የሚገኙ ተፈናቃዮችን በሚመለከት አፋጣኝ ድጋፍ የሚሹትን በመለየት ዝርዝር እቅድ አዘጋጅቶ ማስፈጸም ይገባልም ማለታቸውንም ያካተተው ዘገባው የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም የመሸፈን ጉዳይ የሉዓላዊነትና የክብር ጉዳይ ነው ማለታቸውን አስታውቋል።

ክልሎች በየአካባቢያቸው ችግሮች እንዳይከሰቱ ሲከሰቱም በራሳቸው አቅም ምላሽ ለመስጠት በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለባቸውም አቶ ደመቀ መናገራቸውን ጠቁሟል።

ዘገባው በተጨማሪም የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም “ሰብዓዊ ድጋፍ፣ ገመናና ሉዓላዊነት፣ ፈተናዎችና የመውጫ መንገዶች” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ የመወያያ ፅሁፍ ማቅረባቸውን አስታውቋል።

በፅሁፋቸውም ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዓመታት አደጋ ባጋጠማት ጊዜ ሁሉ በተረጂነት መቆየቷን ጠቅሰው ይህም ሉዓላዊነታቸው ምልዑ እንዳይሆን አድርጓል ማለታቸውን ጠቁሞ በመሆኑም ክብራችንን ለማስጠበቅና ከተረጂነት ለመላቀቅ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎታችንን በራስ አቅም መሸፈን እንደሚገባ ማሳሰባቸውን አካቷል።

በስብሰባው የተሳተፉ ሚኒስትሮች በበኩላቸው እንደ ሀገር የሚያጋጥሙ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን ሃገሪቱ የመቋቋም እምቅ አቅም ቢኖራትም ወደ ተግባር አለወጥነውም ማለታቸውን ጠቅሶ ለአብነትም የተሟላ የመስኖ መሰረተ ልማት የተዘረጋለት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን የለማው 65 በመቶው ብቻ መሆኑን ያነሱት የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ መናገራቸውን አካቷል። በመሆኑም ቀሪ ያለማውን መሬት በመንግስት ደረጃ እንዲለማ በማድረግ ሀገራዊ የመጠባበቂያ እህል ክምችትን ማስፋት ተገቢ ነው ማለታቸውንም አስታውቋል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button