ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ በጎፋ ዞን በደረሰ የመሬት ናዳ አደጋ የሟቾች ቀጥር ከ146 በላይ መድረሱ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16/ 2016 ዓ/ም፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ትላንት ረፋድ 4 ሠዓት አካባቢ በተከሰተው የመሬት ናዳ የሟቾች ቀጥር ከ146 በላይ መድረሱ ተገለፀ።

የዞኑ የመንግስት ረዳት ተጠሪና የፖለቲካና ሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ እና አስቸኳይ የአደጋ ጊዜ መልሶ ማቋቋሚያ ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሀብታሙ ፌተና አደጋውን አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም እስካሁን በተደረገው ፍለጋ ሴቶችና ሕፃናትን ጨምሮ የ 146 ሰዎች አስክሬን ተገኝቷል ብለዋል። ከሟቾች መካከል ሴቶች 50 ሲሆኑ 96 የሚሆኑት ወንዶች ናቸው ተብሏል። 

የአስክሬን ፍለጋ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን የተገለጸ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል አቶ ሀብታሙ ተናግረዋል።

በፍቃደኝነት በነፍስ አድን ስራ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው ካሳሁን አባይነህ ፤ ናዳው ሌሊት በጣለው ከባድ ዝናብ የተከሰተ መሆኑን ገልጾ በአደጋው የተጎዱ ሰዎችን ለመታደግ እንዲሁም በአስከሬን ፍለጋ ሂደት ውስጥ ተሰብስበው በነበሩ ሰዎች እንዲሁም የፀጥታ አካላት ላይ በድጋሚ ጠዋት በደረሰ ናዳ ምክንያት ተጨማሪ ሞት መከሰቱን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጿል። 

“ቤተሰቦቻቸው የተገኙ አስከሬኑን እየወሰዱ ነው:: ቤተሰቦቻቸው ያልተገኙትን ግን ጉድጓድ ቆፍረን እየተቀበሩ ነው:: በፍለጋ ሂደት ውስጥ 10 ሰዎች በህይወት ያገኘን ሲሆን ወደ ሳዎላ ጤና ጣቢያ እና ወደ ወረዳው ወደ ሚገኙ ጤና ጣቢያዎች ተወስደዋል:: ርብርቡ አሁንም ቀጥሏል::” ብሏል።

ሌላኛው በነፍስ አድን ስራ ላይ እየተሰማራ ያለው ወጣት የሟቾች ቁጥር በየሰዓቱ እየጨመረ መሆኑን ጠቅሶ የሟቾች ቁጥር 157 ደርሷል ብሏል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የተገኙት አስከሬኖች ድንኳን ውስጥ እየተሰበሰበ ሲሆን ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ቀብር ስነ ስርዓቱ ይፈፀማል ሲል አክሎ ገልጿል። “ፍለጋው እየተካሄደ ያለው ጠፍቷል ተብለው የተገለጹ ሰዎች ቤተሰቦቻቸው ሲያመለክቱ ሲሆን ከአንድ ቤተሰብ 5፣ 6 ሰው የጠፋበት አለ። ማሽኖች ባለመኖራቸው በአካፋ ነው እየሰራን የምንገኘው ይህም ፍለጋውን አዳጋች አድርጎታል” ብሏል። አስ

የአርታዒ ማስታወሻ፡ ይህ ዜና ከታተመ በኋላ ተጨማሪ መረጃዎች ተካተዋል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button