ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ ብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም 850 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል አለ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 13/2016 ዓ.ም፡- የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም 850 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልግ ብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ገለጸ። የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን የኮሙኒኬሽንና ዓለምአቀፍ ትብብር ዳይሬክተር አቶ ልዑልሰገድ በላይነህ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በስምንት ክልሎች 371 ሺህ 971 የቀድሞ ታጣቂዎች መኖራቸውን እና እነዚህን የቀድሞ ታጣቂዎች መልሶ ለማቋቋም 850 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በመጀመሪያው ዓመት 50ሺ ከትግራይ እንዲሁም 25ሺህ ከሌሎች ክልሎች በአጠቃላይ 75 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማደራጀት ዕቅድ ተይዞ እንደነበረ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ዕቅዱን ለማሳካት የገንዘብ ችግር አጋጥሟል ብለዋል።

እቅዱን ዝቅ በማድረግ 50 ሺ የትግራይ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማደራጀት ዕቅድ ቢያዝም ለሥራው የሚያስፈልገውን 162 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማግኘት ባለመቻሉ ኮሚሽኑ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ መቸገሩን ገልጸዋል። የሚፈለገው ገንዘብ የሚገኝ ከሆነ በመጪው ጥር ወር ዕቅዱ እንደሚተገበር ጠቁመዋል፡፡

274 ሺህ የሚጠጉትና 75 በመቶ የሚሆኑት የቀድሞ ታጣቂዎች በትግራይ ክልል የሚገኙ መሆኑን ጠቁመው፤ ቀሪዎቹ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ በቀድሞው ደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ክልሎች እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

የቀድሞ ታጣቂዎቹን መልሶ ለማቋቋም የሚያስፈልገው 850 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ታጣቂዎቹን ከማደራጀት ጀምሮ ከኅብረተሰቡ ጋር እስከመቀላቀል ድረስ ለሚሆነው ሥራ የሚውል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ያጋጠመውን የገንዘብ ችግር ለመቅረፍና በአፋጣኝ ወደ ሥራ ለመግባት ኮሚሽኑ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አምባሳደሮች ጋር እየተወያየ መሆኑን ያመላከቱት አቶ ልዑልሰገድ፤ ኮሚሽኑ አሁን ላይ አደረጃጀት የመፍጠር፣ የሰው ኃይል የማሟላት፣ የሥልጠና ሰነዶችን የማዘጋጀት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቀድሞ ታጣቂዎቹን ለማቋቋም ዕቅድ ሲታቀድ 85 በመቶ የሚሆነውን ገንዘብ ከዓለም አቀፍ ተቋማትና ለጋሽ ድርጅቶች ለማግኘት እንዲሁም 15 በመቶ የሚሆነውን ከመንግሥት ለማግኘት ታቅዶ እንቅስቃሴ መጀመሩን አውስተው፤ ባለው አጠቃላይ ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አሁን ላይ ብሩ እንዳልተለቀቀ ገልጸዋል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ዓለም አቀፍ ተቋማት በሰላም ስምምነቱ ወቅት የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡ ቢሆንም እስከ አሁን ያደረጉት ድጋፍ ከቢሮ ማደራጀት ተግባር የሚበልጥ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button