ዜና፡ የኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነት ወደ ሁኔታ የማይፈታው ስልታዊ ትብብር እና ወዳጅነት አድጓል ሲሉ ፕሬዝዳንት ሺ ጂፒንግ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6/2016 .ም፡ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በቤጂንግ ከቻይናው ፕሬዝዳን ዢ ጂንፒግ ጋር መገናኘታቸው ተገለጸ። በቤጂንግ በሚካሄደው የቻይና ቤልት ሮድ ሶስተኛው አለም አቀፍ ትብብር ፎረም ላይ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ በተጓዳኝ ከሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው በሁለትዮሽ ግንኙነት እና ትብብር ዙሪያ በመምከር ላይ መሆናቸውን የቻይና መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል። ሁለቱም መሪዎች ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ የጋራ መግለጫ ማውጣታቸውን የጠቆሙት ዘገባዎቹ በጋራ መግለጫቸውም በማንኛውም ወቅቶች የሚተገበር እስትራቴጂያዊ አጋርነት ለመመስረት መስማማተቸውን አመላክተዋል። ባለፉት አስርት አመታት በቤልት ኤንድ ሮድ የትብብር ማዕቀፍ ኢትዮጵያ እና ቻይና የነበራቸው ትብብር በአፍሪካ ቻይና የትብብር ማእቀፍ ቀዳሚው የትብብር መስክ መሆኑን እና ውጤት ያስመዘገበም ነው ሲሉ የቻይናው ፕሬዝዳን ዢ መናገራቸውን ዘገባዎቹ አስታውቀዋል።

ሁለቱ ሀገራት የመሰረቱትን በማንኛውም ወቅቶች የሚተገበር እስትራቴጂያዊ አጋርነትን የጋራ ልማትን ለማፋጠን እና ሁሉም አሸናፊ ሊያደርግ የሚችል ትብብር ለማድረግ ሊጠቀሙበት ይገባል ሲሉ ፕሬዝዳንት ዢ መናገራቸውን ዘገባዎቹ አመላክተዋል።

የጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ጽ/ቤት የሁለቱን መሪዎች ውይይት አስመልክቶ በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጹ ባሰራጨው መረጃ በሁለትዮሽ ውይይቱ ወቅት ፕሬዝዳንት ሺ በኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀል ሁነት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንኳን ደስ ያለዎ ማለታቸውን ጠቁሟል። የኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነትም ከሁሉን አቀፍ ፅኑ ግንኙነት ወደ ሁኔታ የማይፈታው ስልታዊ ትብብር እና ወዳጅነት (All Weather Strategic Cooperation Partnership) ደረጃ ከፍ ማለቱን በይፋ አብስረዋል ያለው ጽ/ቤቱ ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አድንቀው ከቻይናው አረንጓዴ ልማት ፖሊሲ ጋር ተናባቢ በመሆኑ የግሪን ቤልት እና ሮድ አካል ሆኖ ሊደገፍ እንደሚችል ማረጋገጣቸውን አመላክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቻይና ኢንቬስትመንት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እመርታ የሚኖረውን አስተዋፅዖ ማንሳታቸውን እና በተለይም በአምስቱ ቁልፍ ምሰሶዎች-በግብርና ማኑፋክቸሪንግ አይሲቲ ማእድን ልማት እና ቱሪዝም ተጨማሪ ኢንቬስትመንት እንዲኖር የማበረታቻ ጥሪ ማቅረባቸውን ጠቁሟል።

በተመሳሳይ ጠ/ሚኒስትር አቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቻይናው ጠ/ሚኒስትር ሊ ኬ ያንግ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን ጽ/ቤታቸው በማህበራዊ ሚዲያ ፌስቡክ ገጹ ያጋራው መረጃ አመላክቷል። ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከቻይናው አቻቸው ጋር በነበራቸው ውይይት ወቅትም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የምጣኔ ኃብት ትብብር ግንኙነት ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል።

በተጨማሪም የሁለቱ ሀገራት ጠ/ሚኒስትሮች በታደሙበት በተለያዩ መስኮች አስራ ሁለት ያህል የትብብር ስምምነቶች እና ሁለት የፍላጎት ሰነዶች መፈራረማቸውን የጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታውቋል። አስ

Exit mobile version