ዜና፡ አለም አቀፉ መርማሪ ቡድን በኢትዮጵያ የስራ ግዜ እንዲራዘም የአሜሪካን መንግስት ሁሉንም ጥረቶች እንዲያደርግ የኮንግረስ አባላቱ ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10/2016 .ም፡ ስድስት የአሜሪካ የኮንግረስ አባላት ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እና በመንግስታቱ ድርጅት የአሜሪካ ተወካይ በጻፉት ደብዳቤ በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን እንዲመረምር የተቋቋመው አለም አቀፍ የባለሞያዎች ቡድን የምርመራ ግዜ እንዲያራዝም ጥረት እንዲደረግ ጠይቀዋል።

ሳራ ጃኮብስ፣ ኢሃን ኦማር፣ ብራድ ሼርማን፣ ዳንየል ኪልዲ፣ ሊዮይድ ዶጌት እና ጄምስ ማክገቨርን በጋራ ለውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ሀላፊ ለአንቶኒ ብሊንከን እና በመንግስታቱ ድርጅት የአሜሪካ ተወካይ ለሆኑት ሊንዳ ቶማስ በጻፉት ደብዳቤ የመርማሪ ቡድኑ የስራ ግዜ እንዲራዘም እና የትግራይ እና ኦሮምያ ክልሎችን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ የተፈጸሙ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች በመመርመር ፍትህ እና ተጠያቂነትን በማስፈን ተጎጂዎች እንዲካሱ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የኮንግረስ አባላቱ በደብዳቢያቸው ያለ አሜሪካ እና አጋሮቿ ያላሰለሰ ጥረት የመርማሪ ቡድኑ የስራ ግዜ የመራዘም እድል እንደሌለው ጠቁመው የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ የሚከተለው ሁለትዮሽ ግንኙነት ፍትህ እና ተጠያቂነትን ማዕከል ያደረገ መሆን ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል።

በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም የተፈረመው የሰላም ስምምነት የጥይት ድምጽን ቢያስቀረም ግጭቱ አለማብቃቱን መርማሪ ቡድኑ ያወጣው ሪፖትርት ማመላከቱን የጠቆሙት የኮንግረስ አባላቱ በትግራይ ክልል አሁንም የሰብአዊ መብት ጥሰቱ እና የሚፈጸሙ ግፎች ቀጥሏል፣ በአማራ ክልልም የጦር ወንጀል መፈጸሙን የሚያሳዩ አዳዲስ ማድረጃዎች ገሃድ መውጣት ጀምረዋል ሲሉ ገልጸዋል።

ግፍ የፈጸሙ አካላት በስልጣን ላይ እያሉ ኢትዮጵያ በሀገር ደረጃ ተጠያቂነትን ሊያመጣ የሚያስችል የፍትህ ሂደት ታደርጋለች የሚል እምነት እንደሌላቸው የጠቆሙት የኮንግረስ አባላቱ መረጋጋቷን በማስጠበቅ ተጠያቂነት ማስፈን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ብቸኛው ገለልተኛ የሆነው የምርመራ ሂደት የሚያከናውነውን የባለሞያዎች ቡድን የስራ ግዜ ማራዘም ወሳኝ መሆኑን የኮንግረስ አባላቱ በደብዳቤያቸው ጠቁመዋል።  

ከቀናት በፊተ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በተመሳሳይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን እንዲመረምር ያቋቋመውን የባለሞያዎች ቡድን የምርመራ ግዜ እንዲያራዝም መጠየቁን መዘገባችን ይታወሳል። አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪው ተቋም አምነስቲ ባወጣው መግለጫ አሁንም በሀገሪቱ ቀውሶች እየተስፋፉ ይገኛሉ ሲል መግለጹም በዘገባው ተካቷል። 

በኢትዮጵያ የጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እንደቀጠለ ነው ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለሞያዎች ቡድን ትላንት መስከረም 7 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።

በፌደራል መንግስቱ እና በትግራይ ሀይሎች መካከል የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ከአንድ አመት በኋላ የአለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ኤክስፐርቶች በኢትዮጵያ (ICHREE) ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት በኢትዮጵያ አሁንም የጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እንደቀጠለ ነው፤ በሀገሪቱ ሰላም ሰፍኗል ለማለት አስቸጋሪ ነው ሲል መግለጹም በዘገባው ተካቷል።

በአለማችን ከፍተኛ ተጽኖ ፈጣሪ የሆኑ ታላላቅ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በጋራ በመሆን የመንግስታቱ ድርጅት በኢትዮጵያ የሚያካሂደውን የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲመረምር ያቋቋመውን ቡድን ተልዕኮን ለተጨማሪ አንድ አመት እንዲያራዝም መጠየቃቸውን የተመለከተ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል። አስ

Exit mobile version