ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ የሰላም ስምምነቱ ከተደረሰ በኋላ ​​​የኤርትራ ወታደሮች በተቆጣጠሯቸው የትግራይ ግዛቶች የጦር ወንጀል ፈጽመዋል ሲል አምነስቲ ኮነነ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 30/2015 .ም፡ በፌደራል መንግስቱ እና በትግራይ ሀይሎች መካከል በፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ የትግራይ ግዛቶችን ለቀው ያልወጡት የኤርትራ ወታደሮች በሀይል በተቆጣጠሯቸው የትግራይ ይዞታዎች በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም ወንጀል ተደርጎ ሊቆጠር የሚችል የጦር ወንጀል ፈጽመዋል ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው አዲስ ሪፖርት አስታወቀ። ስምምነቱ ከመደረሱ በፊትም ተመሳሳይ ወንጀል የኤርትራ ወታደሮች ይፈጽሙ እንደነበር አውስቷል።

ከሰላም ስምምነቱ በኋል የኤርትራ መከላከያ ሀይሎች በሲቪላውያን ላይ ከፍርድ ሂደት ውጭ የዘፈቀደ ግድያ መፈጸማቸውን ያመላከተው አምነስቲ ሴቶችን በማገት ለወራት ያክል በማቆየት አስገድዶ ግንኙነት የመፈጸም ወንጀል መስራታቸውንም አጋልጧል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ ምርመራ እንዲያካሂድ ያቋቋመው አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ባለሞያዎች ኮሚሽን ስልጣንን እንዲራዘም በማድረግ በአለም አቀፍ ህግ ሊያስጠይቁ የሚችሉ ወንጀሎችን መፈጸማቸውን የሚያመላክቱ ማስረጃዎችን እንዲያጠናቅር በማድረግ ተጠያቂነትን ለማስፈን ለሚደረገው ጥረት እገዛ እንዲያደርጉ አሳስቧል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኤርትራ መንግስት ወታደሮች ከሚያደርሱት በደል ያመለጡ ሰዎችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን እና ምስክሮችን በማነጋገር ያገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የኤርትራ ወታደሮች በማሪያም ሸዊቶ በተባለ ወረዳ 20 ሰዎችን አብዘሃኛዎቹ ወንዶች የሆኑ መግደሉን በአብነት አስቀምጧል። የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ባሉት ሶስት ወራት የኤርትራ ወታደሮች ኮኮብ ጽባህ በተባለ ወረዳ ሴቶችን በተደጋጋሚ ይደፍሩ እንደነበር እና 24 ንጹሃንን በዘፈቀደ መግደላቸውንም ያገኘው መረጃ ማመላከቱን አካቷል።

ምንም እንኳ በፌደራል መነግስት እና በትግራይ ሀይሎች መካከል የሰላመ ስምምነት ቢፈረምም በትግራይ ተወላጅ ንጹሃን ላይ የሚደርሰው አሳዛኝ ጥቃት እንደቀጠለ ነው ሲሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር ቲገረ ቻጉታህ መናገራቸውን ሪፖርቱ አስታውቋል።

አምነስቲ ያነጋገራቸው በኮከብ ጽባህ እና ማርያም ሸዊት ወረዳዎች የሚኖሩ ከጥቃቱ የተረፉ ነዋሪዎች በኤርትራ ድንበር አቅራቢያ ስለሚኖሩ ጥቃቱን የፈጸሙት የኤርትራ ወታደሮች መሆናቸውን በቀላሉ እንደሚለዯቸው አስታውቀዋል ብሏል።  

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያነጋገራቸው ከተፈጸመባቸው አስገድዶ መደፈር እና የጾታዊ ግንኙነት ባርነት የተረፉ አስራ አንድ የሚሆኑ የኮከበ ጽባህ ነዋሪ ሴቶች እንዳስታወቁት የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ አርባ የሚደርሱ ሴቶች በግድ ተደፍረዋል የጾታዊ ግንኙነት እንዲፈጽሙ በባሪያነት አገልግለዋል። አንዳንዶቹ ሴቶች የተደፈሩት በኤርትራ መከላከያ ሀይሎች ካምፕ ውስጥ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ አስገድዶ መደፈር የተፈጸመባቸው በቤቶቻቸው መሆኑን ሪፖርቱ አመላክቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የትግራይ ሀይሎች ተደብቀው ሊኖሩ ይችላሉ በሚል የቤት ለቤት ፍተሻ በስፋት በማርያም ሸዊቶ እና ኮከበ ጽባህ ወረዳዎች የኤርትራ ወታደሮች ያካሂዱ እንደነበረ በሪፖርቱ የጠቆመው አምነስቲ በዚህም ከህግ አግባብ ውጭ በዘፈቀደ ንጹሃንን ገድለዋል በተለይም ወንዶችን ጨፍጭፈዋል ሲል ገልጿል። የግድያዎቹ አፈጻጸም ምንም አይነት አለምቀፍ ግጭት በሌለበት የተፈጸሙ የዘፈቀደ ግድያዎች በመሆናቸው የጦር ወንጀሎች ናቸው ሲል ገልጿል።

አምነስቲ ያነጋገራቸው 49 ከጥቃቱ የተረፉ ነዋሪዎች በተጨማሪም የኤርትራ ወታደሮች ንብረቶቻቸውን እንደዘረፉባቸው መናገራቸውን ሪፖርቱ አካቷል።

በርካታ ወንጀሎች መፈጸማቸውን የሚያመላክቱ ማስረጃዎች አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋሙ አምነስቱ ማሰባሰቡን አስታውቆ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ጉዳዩ በአግባቡ እና አለም አቀፍ መመዘኛዎችን በጠበቀ መልኩ የመመርመር ግዴታ አለባቸው ሲል አሳስቧል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ ምርመራ እንዲያካሂድ ያቋቋመው አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ባለሞያዎች ኮሚሽን ስልጣንን የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ጉባኤ በቀጣይ በሚያደርገው ስብሰባ እንዲራዘም እንዲያደርግ አምነስቲ በሪፖርቱ ጠይቋል።

በተጨማሪም አምነስቲ የአፍሪካ ህብረት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን እንዲመረምር ያቋቋመውን እና በቅርቡ በይፋ ስልጣኑ እንዲያበቃ ውሳኔ ያስተላለፈበትን የመማሪዎች ቡድን ውሳኔውን እንዲያጤነው ጠይቋል። የመርማሪ ቡድኑ ስራ እንዲቋረጥ የአፍሪካ ህብረት የሰብአዊ ኮሚሽን ውሳኔ ያሳለፈው ቡድኑ ምንም አይነት ሪፖርት ሳያቀርብ መሆኑንም ጠቁሟል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርቱን ለኢትዮጵያ መንግስት እና የኤርትራ መንግስት አስተያየት እንዲሰጡበት ቢልክም ምንም አይነት ምላሽ ከሁለቱም መንግስታት እንዳልተሰጠው በሪፖርቱ አስታውቋል።

የኤርትራ ወታደሮች የሰላም ስምምነቱ ከተደረሰ በኋላ በትግራይ ሰሜን ምስራቅ ክፍል በሚኖሩ የኢሮብ ብሔር ተወላጆች ላይ ተመሳሳይ ወንጀሎች እየፈጸሙ እንደሚገኙ አዲስ ስታንዳርድ በአከባቢው ከሚገኙ ነዋሪዎች ያገኘውን መረጃ አመላክቷል። የኢሮብ ተወላጆችን በማገት እንደሚወስዱ እና ሴቶች ላይ አስገድዶ መድፈር እንደሚፈጽሙ ነዋሪዎቹ ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቀዋል። የአከባቢው ባለስልጣናት 28 የአከባቢው ተወላጅ የሆኑ ወጣቶች በኤርትራ ሀይሎች ታፍነው መወሰዳቸውን ገልጸዋል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button