ዜናፖለቲካ

ዜና፡ የአማራ ክልል መንግስት የኃይል አማራጭን በመተው ወደ ሰላም ለሚመለሱ ኃይሎች የሰላም ጥሪ አስተላለፈ 

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 2/ 2016 ዓ/ም፦ የአማራ ክልል መንግስት ከኃይል አማራጭን በመተው ወደ ሰላም ለሚመለሱ ኃይሎች የሰላም ጥሪ አስተላልፏል።

የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር መንገሻ ፈንታው የክልሉ መንግስት ያወጣውን የሰላም ጥሪ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ የሰላም ጥሪው “ተጨማሪ ደም መፋሰስን ለማስቀረት መንግስት በሆደ ሰፊነት የከፈተው የሰላም በር ነው” ሲሉ ተናግረዋል። አሁን ላይ በክልሉ ህገ መንግስታዊ ስርአቱን መታደግ በመቻሉና፣ የክልሉ ሰላም ሁኔታ በእጅጉ እየተሻሻለ በመምጣቱ ይህንንም ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የሰላም ጥሪ ማድረግ አስፈልጓል ብለዋል። 

በመሆኑም ይህ ጥሪ ለህዝብ ይፋ ከተደረገ ጀመሮ በሚቆጠር ሰባት ቀናት ውስጥ በየትኛውም ኢመደበኛ አደረጃጀት እና ትጥቅ ትግል ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ ታጣቂዎች ባሉበት አካባቢ በሚገኙ የኮማንድ ፖስት አዛዦች ለዚሁ አላማ ለይተው ለህዝብ ወደሚያሳውቋቸው የመሰብሰቢያ ስፍራዎች በመሄድ ወደ ሰላማዊ ህይወት ለመመለስ ያላቸውን ፍላጎት እንዲያሳውቁ ጥሪ ቀርቧል።

ለህግ እና ፍትህ አካላት የተሃድሶ መርሃግብር ማጠናቀቂያ የምስክር ወረቀት ያገኙ የቀድሞ ታጣቂዎች በግጭቱ አውድ ውስጥ የተፈፀሙ በምህረት ሊሸፈኑ የሚችሉ ወንጀሎችን በተመለከተ የምህረት ተጠቃሚ እንደሆኑ በመገንዘብ እነዚህ ግለሰቦች ላይ ከነዚህ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ የተጀመሩ የምርመራ፣ የክስም ሆነ የፍርድ ማስፈፀም ሂደቶችን በማቋረጥ ተገቢውን ትብብር እንዲያደርጉ መመሪያ ተላልፏል ተብሏል።

የክልል፣ ዞን፣ ወረዳ እና ቀበሌ የፖለቲካ፣ የአስተዳደር አካላት እና አመራሮች ይህን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ለሚመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ኑሮ መመለስ እንዲችሉ ተገቢውን ትብብር እንዲያደርጉ፣ በተለይም እነዚህ ዜጎች በሰላማዊ እና ህጋዊ አግባብ የፖለቲካ ግብ እና አጀንዳቸውን ማራመድ ይችሉ ዘንድ ምቹ አውድ እና የውይይት መደረኮችን እንዲያመቻቹ መመሪያ ተሰጥቷል።

በዚሁ አጋጣሚ ይህን ጥሪ ቸል በማለት የአመፅ እና የጉልበት መንገድ በሚመርጡ ግለሰቦች እና ታጣቂዎች ላይ የተጀመረው የህግ ማስክበር እርምጃ ተጥናክሮ እንደሚቀጥል ከኢቢሲ የተገኘው መረጃ አመላክቷል።አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button