ማህበራዊ ጉዳይቢዝነስዜና

ዜና፡ የአሳይታ- አፋምቦ-ጅቡቲ ድንበር መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት መጠናቀቁ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 21/2016 ዓ.ም፡- ወደ ጅቡቲ ለመጓዝ አገልግሎት በመስጠት ላይ ከሚገኘው የጋላፊ መስመር በተጨማሪ ሌላ አማራጭ ሆኖ የሚያገለግለው የአሳይታ-አፋምቦ-ጅቡቲ ድንበር መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለትራንስፖርት አገልግሎት ክፍት መሆኑ ተገለጸ።

መንገዱ በዋናነት ኢትዮጵያን በአሳይታ በኩል ከጅቡቲ ጋር በቅርበት ከማስተሳሰር ባለፈ የሀገራችንን የገቢ እና ወጪ ንግድ በማቀላጠፍ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንደሚኖረው የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በማህበራዊ ትስስር ፌስቡክ ገጹ ባጋራው መረጃ ጠቁሟል።

ከዚህ በተጨማሪም አሳይታ ከተማን ከአፋምቦ ወረዳ ብሎም በርካታ ቀበሌዎችን በማገናኘት የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን ይበልጥ ያጠናክራል ሲል አስታውቋል።

በተጨማሪም ይህ መስመር አሁን ላይ ያለውን ሚሌ – ዲቼ ኦቶ-ጋላፊ-ጅቡቲ ወደብ ያለውን መንገድ በ 30 ኪሎ ሜትር ያሳጥረዋል ያለው የአስተዳደሩ መረጃ ወደፊት በአካባቢው ሊመረቱ የሚችሉ የፋብሪካ ውጤቶችን (ስኳር ፣ የስንዴ ዱቄት) ወደ ውጪ ገበያ ለማቅረብ ፋይዳው የጎላ እንደሚሆን አመላክቷል።፡

የፕሮጀክቱ ዋና ዋና ስራዎች ሙሉ በሙሉ መጠናቀቃቸውን፣ የትራፊክ ምልክቶች ተከላ፣ የቀልም ቅብ ስራዎች እና ሌሎች ጥቃቅን ስራዎችም መገባደዳቸውን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ያጋራው መረጃ ያሳያል።

የመንገዱን ግንባታ ለማከናወን የተመደበው ከ1 ነጥብ ስድስት ቢለየን ብር በላይ የሆነው ወጪ ሙሉ ለሙሉ የተሸፈነው በኢትዮጵያ መንግስት መሆኑን የጠቆመው የመንገዶች አስተዳደር የመንገዱ ርዝማኔ 50.34 ኪሎ ሜትር መሆኑን አስታውቋል።

ግንባታውን ሲያካሂድ የቆየው ሀገር በቀሉ የስራ ተቋራጭ አሰር ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መሆኑን ያመላከተው የአስተዳደሩ መረጃ የማማከርና የቁጥጥር ስራውን ደግሞ ይዲዲያ ኢንጅነሪንግ ኮንሰልታንትስ ማከናወኑን ጠቁሟል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በአካባቢው ከዚህ ቀደም ደረጃውን የጠበቀ የመንገድ መሰረተ ልማት ያልነበረ በመሆኑ ህብረተሰቡ በትራንስፖርት እጦት ምክንያት በእግር እና በግመል ከመጓዝ ውጭ ሌላ አማራጭ እንዳልነበረው ተገልጿል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button