ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ የአውሮፓ ህብረት አለም አቀፉ መርማሪ ቡድን በኢትዮጵያን የስራ ጊዜ እንዲራዘም የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ሂዩማን ራይት ዎች ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18/2016 .ም፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን እንዲመረምር ያቋቋመውን አለም አቀፍ የባለሞያዎች ቡድን የምርመራ ግዜ እንዲያራዝም ሂዩማን ራይት ዎች በድጋሚ ጠየቀ። የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ሚና እንደሚጠበቅበትም አመላክቷል።

አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ተቋም ሂዩማን ራይት ዎች ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ በጦርነቱ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸው ተበዳዮች እና የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋማት እውነተኛ ምርመራ እንዲደረግ እና ፍትህ እንዲሰፍን በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን አውስቷል። ተበዳዮችም ሆኑ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች የሀገሪቱ  የፍትህ ተቋማት ፍትህ ያሰፍናሉ የሚል እምነት እንደሌላቸው መግለጫው አስታውቋል።

የአለም አቀፉ የመርማሪዎች ቡድን እንዲቋቋም ከፍተኛ ሚና የተጫወተው የአውሮፓ ህብረት አሁንም የስራ ግዜው እንዲራዘም ረቂቅ ሃሳብ በማዘጋጀት ረገድ የመሪነት ሚና እንዲጫወት ጠይቋል።  

መርማሪ ቡድኑ ረቂቅ የመፍትሔ ሃሳብ ለህብረቱ ጉባኤ ለማቅረብ አንድ ሳምንት እየቀረበውም ቢሆን የአውሮፓ ህብረት ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንደማይታይበት በመግለጽ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪው ተቋም ህብረቱን ተችቷል። በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሁኔታ አጀንዳ እንዳይሆን በማድረግ የተጎጂዎች ተስፋ ማጨለም አግባብ አይደለም ሲል ገልጿል። የመርማሪ ቡድኑ በቅርቡ ባቀረበው ሪፖርት ያስቀመጣቸውን ምክረ ሃሳቦች ለመተግበር በተለይም በሀገሪቱ ተካሂዶ በነበረው ጦርነት እና በአሁኑ ወቅትም በቀጠለው ግጭት የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ቀጣይነት ባለው መልኩ በአለም አቀፍ ደረጃ ሊመረመሩ እንደሚገባ አሳስቧል።

የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት እንዲከበር እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን የሚያስችሉ ተግባራት እንዲፈጽም የጠየቀው ሂዩማን ራይት ዎች ለዚህም የመርማሪ ቦርዱ የስራ ግዜ እንዲራዘም በማድረግ ምርመራዎች እንዲቀጥሉ እና ምክረ ሃሳቦች እንዲተገበሩ እንዲሁም ሪፖርቶች ይፋ እንዲቀርቡ በማስቻል የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ አሳስቧል።

ይህን አለማድረግ ግን የቆመለትን አላማ እንደመተው የሚቆጠር ይሆናል ሲል አስጠንቅቋል።

በቅርቡ በተመሳሳይ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አለም አቀፉ የባለሞያዎች ቡድን የምርመራ ግዜ እንዲያራዝም መስከረም 7 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ መጠየቁን መዘገባችን ይታወሳል። አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪው ተቋም አምነስቲ ባወጣው መግለጫ አሁንም በሀገሪቱ ቀውሶች እየተስፋፉ ይገኛሉ ሲል መግለጹን፣ የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት አባል ሀገራት የአለም አቀፉን የመርማሪዎች ቡድን የስራ ግዜ በማራዘም በሀገሪቱ ላይ አለምአቀፍ ትኩረት እንዲደረግ ማስቻል አለበት ሲል ማሳሰቡም በዘገባው ተካቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በፌደራል መንግስቱ እና በትግራይ ሀይሎች መካከል የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ከአንድ አመት በኋላ የአለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ኤክስፐርቶች በኢትዮጵያ (ICHREE) ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት በኢትዮጵያ አሁንም የጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እንደቀጠለ ነው ማለቱን እና በሀገሪቱ ሰላም ሰፍኗል ለማለት አስቸጋሪ ነው ሲል ቡድኑ በሪፖርቱ ማስጠንቀቁን መዘገባችን ይታወሳል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button