ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ የኢትዮጵያ መከላከያ የአልሸባብን ጥቃት በመመከት ደምስሸዋለሁ ሲል ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9/2016 .ም፡ አልሸባብ በሶማሊያ ሮብ ድሬ በተባለ ቦታ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ለመፈፀም ቢያስብም እንዳልተሳካለት እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በወሰደው እርምጃ መደምሰሱ ተገለጸ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ባስተላለፈው መልዕክት የጥፋት እጁን ያልሰበሰበው አልሸባብ በሶማሊያ ሮብ ድሬ በተባለ ቦታ ተደመሠሠ ሲል አስታውቋል።

በሶማሊያ በአከባቢው የሰፈረው ክፍለጦር አዛዥ የሆኑት ኮሎኔል ፈይሳ አየለ የአልሸባብ ሃይል ሶስት ፈንጂ የጫኑ መኪናዎችን እና 12 ፈንጂ የታጠቁ ታጣቂዎቹን እንዲሁም ከ450 በላይ አሉኝ የሚላቸዉን አባላቱን ለጥፋት ቢያሰልፍም በቀጠናው በሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት የጥፋት ሃሳቡን ሳያሳካ መደምሰሱን መናገራቸውን በፌስቡክ ገጹ ባሰፈረው መረጃ አካቷል።

በሶማሊያ ከሰፈረው የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት አመራሮች መካከል አንዲ የሆኑት ሻምበል ጥላሁን ደምሴ በበኩላቸው አልሸባብ በርካታ የሠው ሃይል አሠልፎ በሠው እና በተሽከርካሪ ፈንጅ ጠምዶ ጥቃት ለመፈፀም ቢንቀሳቀስም ሁለት ክፍሎች በመናበብ እና በመቀናጀት ለጥፋት የተንቀሳቀሰውን የአልሸባብ ሃይል ቀደምተኝነትን በመዉሰድ ከአፈር ቀላቅለነዋል ማለታቸውንም የኢትዮጵያ መካላከያ ሰራዊት በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ባስተላለፈው መልዕክቱ ተካቷል።

አሁንም የሽብር ቡድኑ አልሸባብ ያለበት ቦታ ድረስ እግር በእግር በመከታተል እየለቀምነው ሲሉ ሻምበል ጥላሁን ደምሴ መናገራቸውን ያስታወቀው የኢትዮጵያ መከላከያ አልሸባብን በማጥፋት የቀጠናውን ሠላም እናረጋግጣለን ማለታቸውንም አመላክቷል።

በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ቀናት አልሸባብ በርካታ የኢትዮጵያ ወታደሮችን ገደልኩ፣ ማረኩ ሲል መግለጹን ሮይተርስ የዜና ወኪልን ዋቢ በማድረግ መዘገባችን ይታወሳል።

የሩሲያው ስፑትኒክ ሚዲያ በድረገጹ አልሸባብ በፈጸመው ጥቃት 167 የኢትዮጵያ ወታደሮችን ገደልኩ ማለቱን የሶማሊያ መገናኛ ብዙሃንን ዘገባ ዋቢ በማድረግ አስታወቁን እና ከጥቃቱ የተረፉትንም ማርኪያለሁ ማለቱንም በዘገባችን ተካቷል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button