ዜናፖለቲካ

ዜና፡ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት “የሰላም አማራጭን” ባለመቀበሉ በቡዱኑ ላይ የተጠናከረ ርምጃ እየተወሰደ ነው፤ ለሰላማዊ ውይይት በራችን ክፍት ነው_ የኦሮሚያ ክልል መንግስት

አዲስ አበባ፣ ህዳር 22/ 2016 ዓ/ም፦  የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የቀረበለትን “የሰላም አማራጭ ወደ ጎን ብሎ በሽብር ተግባሩ በመቀጠሉ” መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በቡድኑ ላይ የተጠናከረ ርምጃ እየወሰደ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል መንግስት አስታወቀ፡፡ ታጣቂ ቡድኑ ከሚፈጽመው “የሽብር ተግባር” ተቆጥቦ ወደ ሰላማዊ መንገድ የሚመጣ ከሆነ መንግሥት ሁልጊዜም ለሰላም በሩ ክፍት መሆኑን የክልሉ መንግስት ገልጿል፡፡

የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን የቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት ገለጻ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው ቡድኑ “በተከፈተው የፖለቲካ ምህዳር ባለመጠቀም ኃይልን መሠረት ያደረገ የትጥቅ ትግል አንስቶ ባለፉት ዓመታት በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ የተለያዩ ጉዳቶችን አድርሷል” ሲሉ ከሰዋል፡፡ 

መንግሥትም ቡድኑ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመጣ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል ያሉት ኃላፊው ሆኖም “ቡድኑ የሰላም አማራጮችን ወደ ጎን ትቶ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተለያዩ ጉዳቶችን በማድረስ በሽብር ተግባሩ በመቀጠሉ ጠንካራ ርምጃ እየተወሰደበት ይገኛል” ብለዋል፡፡

የቢሮው ኃላፊ መንግሥት ችግሮች እንዲፈቱ በሀገር ሽማግሌዎች፣ በአባ ገዳዎችና በሀደ ስንቄዎች አማካኝነት እርቅ ለመፍጠር ጥረት አድርጓል ብለዋል። ሆኖም ቡድኑ በአባገዳዎች የቀረበለትን ሰላም ጥሪ “ወደ ጎን ትቶ” ሦስተኛ ወገን በተገኘበት ካልሆነ አልደራደርም ማላቱን አውስተዋል።

መንግሥት የሕግ የበላይነትን ማስፈን የዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥ ኃላፊነት ስላለበት የክልሉና የፌዴራል ፀጥታ ተቋማት በቡድኑ ላይ ርምጃ እየወሰዱ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም ቡድኑ ተቆጣጥሯቸው የነበሩ ቦታዎችን የማስለቀቅ ሥራ እየተሠራ ነው በማለት ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት በምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ ቡኖ በደሌ በመንግስት ሃይል በተወሰደበት እርምጃ “ሙትና ቁስለኛ” ሆኗል ብለዋል።

የቢሮው ሓላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ፣ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሺርካ ወረዳ፣ ባሳለፍነው ሳምንት ቡዱኑ ጥቃት መፈጸሙን ገልጸዋል። እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፤ “ቡድኑ አሸባሪ ካስባሉት ጉዳዮች አንዱ የራሱን የመደራደር አቅም ከፍ ለማድረግ ሰላማዊ ዜጎቸ ላይ ያነጣጠረ ርምጃ መውሰዱ ነው”፡፡

መንግሥት ለሰላም የዘረጋው እጁ ዛሬም አልታጠፈም ያሉት አቶ ኃይሉ፤ “ቡድኑ ከተግባሩ ተቆጥቦ ወደ ሰላማዊ ውይይትና ንግግር ከተመለሰ መንግሥት ለሰላም ሁልጊዜም በሩ ክፍት ነው” ብለዋል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ባሳለፍነው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል አርሲ እና ቄለም ውለጋ ዞን በተለያየ ጊዜ በተፈጸሙ ሁለት ጥቃቶች 45 ሰዎች ተገድለዋል። በክልሉ አርሲ ዞን ሺርካ ወረዳ፣ ባሳለፍነው ሳምንት ህዳር 13 እና 17 ቀን ማንነታቸው ባልተለየ ታጣቂዎች በደረሰ ጥቃት 36 የኦሮቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች እንደተገደሉ፣ የስፍራው ነዋሪ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡ 

የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ሓላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ለአሜሪክ ድምጽ ሬድዮ፣ ጥቃቱን የፈጸመው፣ መንግሥት “ኦነግ ሸኔ” ብሎ የሚጠራው ዐማፂ ኃይል መሆናቸውን ገለጸው በጥቃቱም 27 ሰዎች ተገድለዋል ብለዋል፡፡ ኃላፊው አክለውም ቡድኑ ባሳለፍነው ሳምንት ቡድኖ በድሌ ዞን ጫዋቃ ወረዳ ላይ የምንግስት ሀይሎች የወሰዱበትን እርምጃ ለመበቀል ብሎ ነው ጥቃቱን የፈጸመው ሲሉ ገልጸዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button