ዜና

ዜና: የመንግስት የሀገር ውስጥ ብድር ከፍተኛ እየሆነ በመምጣቱ የገንዘብ ሚኒስቴር በቀጣይ የተለየ የፖሊሲ አቅጣጫን በመከተል እንዲሰራ ማሳሰቢያ ተሰጠው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15/2016 ዓ.ም፡- የገንዘብ ሚኒስቴር የመንግስት የሀገር ውስጥ ብድር ከፍተኛ እየሆነ በመምጣቱ በቀጣይ የተለየ የፖሊሲ አቅጣጫን በመከተል መስራት እንደሚገባው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሳቢያ ተሰጠው።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የገንዘብ ሚንስቴርን እና ተጠሪ ተቋማቱን የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወር የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል፡፡

በግምገማው ላይ “የውጭ ሀገር የብድር ጫናን ለመቀነስ ገንዘብ ሚንስቴር አበረታች ስራዎችን አከናውኗል” ሲሉ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ ገልጸው “ነገር ግን የሀገር ውስጥ ብድር ከፍተኛ እየሆነ በመምጣቱ በቀጣይ የተለየ የፖሊሲ አቅጣጫን በመከተል መስራት እንደሚገባ” አመላክተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አብረሃም አለማየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ መንግስት ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በነበረው መልካም ግንኙነት የወለድ ጫና የሌለባቸውን ብድሮች በማግኘት ስኬታማ ስራዎች ሰርቷል ሲሉ ገለጸዋል።

የገንዘብ ሚንስቴር ሚንስትር አቶ አህመድ ሺዴ ባለፉት 9 ወራት የተሰበሰበ ገቢ 331.1 ቢሊዮን፣ ክፍያ ደግሞ 470.0 ቢሊዮን ብር መሆኑን ገልጸው፤ የበጀት ጉድለቱን በሀገር ውስጥ ምንጮች መሸፈን ስለመቻሉ አስረድተዋል።

በአንዳንድ የሀገሪቱ አከባቢዎች ያለው አለመረጋጋት ለሰብዓዊ ድጋፍና መልሶ ማቋቋም የሚጠይቁት ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ በመንግስት በጀት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩንም አቶ አህመድ መግለጻቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

የገንዘብ ሚንስቴር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በፌዴራል መንግስት በጀት ፕሮጀክቶች በሚሰሩበት ጊዜ የተጋነነ የካሳ ክፍያ በመጠየቁ ሀገራዊ ልማቱን የሚያደናቅፍ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

አዲስ የተቋቋሙ ክልሎች ሀገራዊ የፋይናንስ ስርዓቱን ተከትለው እንዲሰሩ ለማስቻል የተለያዩ እገዛዎች ስለመደረጋቸው እዮብ (ዶ/ር) ጠቁመው ክልሎች የራሳቸውን ገቢ በማመንጨት ያለባቸውን የበጀት ክፍተት ማሟላት እንደሚገባቸውም መክረዋል፡፡ አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button