Uncategorized

ዜና: የታገቱ ልጆቻችውን ለማስለቀቅ የተጠየቁት ከፍተኛ ገንዘብ ለጭንቀት እንደዳረጋቸው የታጋች ቤተሰቦች ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3/2016 ዓ.ም፡-ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ በታጣቂዎች ታፍነው ከነበሩ ተማሪ ቤተሰቦች ለማስለቀቂያ ከፍተኛ ገንዘብ መጠየቃቸው ለጭንቀት እንደዳረጋቸው አስታወቁ።

ከአማራ ክልል ተነስተው ወደ አዲስ አበባ በአውቶብሶች ሲጓዙ የነበሩ ከ100 በላይ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በታጣቂዎች መታገታቸው መዘገቡ ይታወሳል።

አንድ የሶስተኛ አመት የደባርቅ ዩኒቨርስቲ ተማሪ እሀቷ እንደታገተችባት ለአዲስ ስታንዳርድ ያስታወቀች የታጋች ቤተሰብ ለማስለቀቂያ ግማሽ ሚሊዮን ብር ቤተሰቡ እንዲከፍል መጠየቁን ገልጻለች። በተጠየቁት የገንዘብ መጠን ቤተሰቡ ለከፍተኛ ጭንቀት እና ጫና ተዳርጓል ብላለች።

“እስከ አሁን ድረስ ከመንግሥት ምንም አይነት መፍትሔ አልተሰጠንም” ስትል የገለጸችልን የታጋች ተማሪ ቤተሰብ “ያለን ብቸኛ እና የተሻለው አማራጭ ገንዘቡን ማሰባሰብ እና መክፈል ነው” ሲሉ ተናግራለች።

በተመሳሳይ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሌላ የታጋች ቤተሰብ አባል ለማስለቀቂያ 700,000 ብር መጠየቃቸውን ተናግረው “700ሺ ይቅርና 7ሺ ብር የለንም” ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል::

ቢቢሲ እንደዘገበው አንዳንድ ተማሪዎች ያመለጡ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በኋላ በተወለዱበት አከባቢ ተለይተው እንደተለቀቁ ገልጿል። አሁንም በምርኮ ላይ የሚገኙት ተማሪዎች የት እንዳሉ ግን አይታወቅም።

የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አቶ አስማማው ዘገዬ ድርጊቱን ቢያረጋግጡም ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

አዲስ ስታንዳርድ ከሰሜን ሸዋ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም ከትምህርት ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

“ከቅርብ ግዜያት ወዲህ በተደጋጋሚ በኦሮምያ እና አማራ ክልሎች እየተፈጸሙ ያሉ የንጹሃን እገታዎች፣ የተራዘመ ግጭት ወንጀለኞች እንዲበረታቱ እና የህግ የበላይነትን እንደሚሸረሽር እንደሚያደርግ ማሳያ ነው” ሲሉ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤሪቪን ማሲንጋ መግለጻቸውን በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ይፋ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው 3ኛ አመታዊ የሰብአዊ መብት ሁኔታ ሪፖርቱ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ላይ የሚደርሰው አፈና እየጨመረ መምጣቱን አመልክቷል።

ከዚህ ቀደም አዲስ ስታንዳርድ በጥቅምት 2023 ባቀረበው ዘገባ በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ለገንዘብ ተብሎ የሚካሄደው አፈና እየጨመረ መምጣቱንና ለዚህም በመንግሥት ሃይሎች እና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መካከል የቀጠለው ግጭት መንሰኤ መሆኑን መገለጹ ያታወሳል። አስ

ተጨማሪ አሳይ
Back to top button