ማህበራዊ ጉዳይዜናፖለቲካ

ዜና: የትግራይ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው የመመለሱ ሂደት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል፣ አለምአቀፍ ጫና ይሻል - ሳልሳይ ወያነ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9/2016 ዓ.ም፡- በትግራይ ከሚንቀሳቀሱ እና በምርጫ ቦርድ እውቅና ካገኙ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው ሳልሳይ ወያነ ትግራይ የትግራይ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለሱ ሂደት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል፣ “ጥርጣሬ የተላበሰ ሁኗል” ሲል ገለጸ።

ፓርቲው ባወጣው መግለጫው “ወራሪ ሃይሎች” ሲል የጠራቸው የምዕራብ ትግራይ አከባቢ አስተዳዳሪ አካላት በቅርቡ እየሰጡት ያለው መግለጫ የሰላሙን ሂደት ሊያደናቅፉት ይችላሉ ሲል ስጋቱን አጋርቷል።

“በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የትግራይ ተፋናቃዮች በተጠለሉባቸው አከባቢዎች በክረምቱ ከፍተኛ ዝናብ እና ጎርፍ ሳቢያ በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ” ሲል የገለጸው ሳልሳይ ወያነ “ህገወጥ አስተዳደር” ሲል የገለጸው የምዕራብ ትግራይ አስተዳዳሪዎች ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለሱን ሂደት እያወሳሰቡት ይገኛል ሲል ኮንኗል።

የሳልሳይ ወያነ ፓርቲ መግለጫ የወጣው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት እና የሰላምና ጸጥታ ሴክሬተሪያት ሃላፊ ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ ተከትሎ ነው።

ሌተናል ጀነራሉ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለሱ ተግባር ያልተሳካበት ዋነኛ ምክንያት “በእኛ በትግራይ በኩል አይደለም” ብለዋል። “የአማራ ክልል መንግስት ለማስፈጸም የነበረው ዝግጁነት ዝቅተኛ ስለነበረ” ነው ያሉት ጀነራሉ፣ “የተለያየ ምክንያት በመደርደር፣ የማጓተት ሁኔታዎች ታይተዋል፤ በዚህም ምክንያት ዘግይቷል” ሲሉ ተደምጠዋል።

ተፈናቃዮቹ በመጡባቸው አከባቢዎች “በህገወጥ መንገድ አዲስ ሰፋሪዎች እንዲሰፍሩ መደረጉ እና ታጣቂዎች መኖር” ለመዘግየቱ ከሰጧቸው ምክንያቶ ይገኝበታል።

የተቃዋሚ ፓርቲው ሳልሳይ ወያነ በመግለጫው በሱዳን የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችን ሁኔታ አሳሳቢ ነው ያለ ሲሆን በሱዳን ተቀናቃኝ ሀይሎቸ መካከል በመካሄድ ላይ ያለው ውጊያ ተፈናቃዮቹ በተጠለሉባቸው መጠለያ ካምፕ እየተጠጋ መሆኑ እና በመጠለያ ካምፖቹ ውስጥ በቂ መሰረታዊ ድጋፍ እያገኙ አለመሆኑን ሁኔታዎቹ አስጊ ናቸው ሲል አሳስቧል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ሳልሳይ ወያነ የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እና “በህገ መንግስቱ መሰረት ህጋዊ የሆነ የትግራይ አስተዳደር” እንዲመሰርቱ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ አለም አቀፍ ግፊት እንዲደረግ ጠይቋል::

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button