ዜናህግ እና ፍትህ

ዜና፡ የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ 

አዲስ አበባ ግንቦት 13/ 2016 ዓ/ም፦ የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ያቀረቡትን የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አደረገ።  ተከሳሹ ያቀረቡትን ‘‘ክሱ ይሻሻልልኝ’’ ጥያቄን የያዘው የክስ መቃወሚያ ውድቅ የተደረገው “ክሱን ለማሻሻል የሚያስችል የህግ አግባብነት የለውም” በሚል መሆኑ ተገልጿል

ዛሬ በዋለት ችሎት አቶ ታዬ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ በቀረበላቸው ጥያቄ መሰረት፤ “የጻፍኩት ጽሁፍ ፕሮፖጋንዳ አይደለም፤ ወንጀል አልፈጸምኩም” በማለት የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

አቶ ታዬ ዐቃቤ ህግ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ብቻ ብሎ በክሱ መጥቀሱን ገልጸው፤ “የኦሮሚያ ምክር ቤት አባልና የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ነኝ፤ ይህ ተካቶ ይስተካከልልኝ’’ በማለት አመልክተዋል። 

አቶ ታዬ እጃቸው ላይ አለብኝ ባሉት አለርጂክ ምክንያትም “እጄ ላይ ካቴና እንዳይደረግ ይታዘዝልኝ” በማለት አመልክተዋል።

በተጨማሪም አቶ ታዬ ተይዞብኛል ያሉት ረቂቅ መጽሀፍ፣ ሁለት ሞባይሎች እና አንድ ታብሌት እንዲመለስላቸው አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱም በአቤቱታቸው ላይ ትዕዛዝ እንደሚሰጥበት ገልጿል።

ከሳሽ ዐቃቤ ህግ አቶ ታዬ ክደው የተከራከሩ መሆኑን ተከትሎ ማስረጃዎችና ምስክሮች እንዲሰሙለት ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ለግንቦት 29 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን ተከትሎ በጸጥታ ሀይሎች ታህሳስ 2 ቀን በቁጥጥር ስር የዋሉት የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ታዬ በፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ  ሶስት ክሶች ተመስርቶባቸዋል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በዚህም መሰረት በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 251/ሐ እና አንቀጽ 257/ሰ ስር የተመላከተውን ድንጋጌ እና የጦር መሳሪያ አዋጅን መተላለፍ የሚል ክስ አቅርቦባቸዋል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ሲሰሩ የሀገርን፣ “የመንግስትና የህዝብን ደህንነት ማስጠበቅ ማረጋገጥ ሲገባቸው ይህን ወደጎን በመተው የሽብር ቡድኖችና የፀረሰላም ኃይሎችን የሚደግፉ ፕሮፖጋንዳ መልዕክቶችን በስማቸው በከፈቱት ማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ ሲያስተላልፉ ነበር” የሚል ይገኝበታል፡፡

በተጨማሪም ፍቃድ ሳይኖራቸው የጦር መሳሪያ አዋጁን በመተላለፍ በታህሳስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ከረፋዱ 5:00 ሰዓት ላይ በልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 6 በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በተደረገ ብርበራ አንድ ታጣፊ ክላሽ ከሁለት የክላሽ ካዝና ከ60 የክላሽ ጥይት ጋር ተይዞባቸዋል የሚል ክስ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button