ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ በአማራ ክልል በግጭት ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ትምህርት አለመጀመራቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15/ 2016 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል በ2017 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን በበርካታ የገጠር ከተሞች እና ወረዳዎች የተማሪዎች ምዝገባ አለመካሄዱን እና ትምህርት አለመጀመሩን ተማሪዎች እና ወላጆች ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ በሚገኝ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነ ልጃቸው በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ትምህርት አለመጀመሩን ለአዲስ ስታንዳርድ የገለጹ ወላጅ፤ በአከባቢያቸው “ሁሉም በሚባል ደረጃ ትምህርት ቤቶች በጸጥታ ችግር ምክንያት መዘጋታቸውን” ተናግረዋል።

“ባለፈው አመትም በተመሳሳይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ሳይከታተሉ ነበር ያሳለፉት” ያሉት የተማሪ ወላጅ አክለውም “በወረዳው የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ወደ ወታደራዊ ካምፕ መቀየራቸውን” ጠቁመዋል።

በማዕከላዊ ጎንደር ደምበያ ወረዳ አይምባ ቀበሌ በሚገኝ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪ የነበረው ከፍያለው በበኩሉ በአከባቢው ትምህርት ከተቋረጠ መሰንበቱን ለአዲስ ስታንዳርድ አረጋግጧል።

“በእኛ ቀበሌ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በሙሉ ዝግ ናቸው። በአከባቢው ባለው ግጭት የተነሳ የወደሙ ትምህርት ቤቶች አሉ” ያለው ከፍያለው አክሎም አሁን ላይ በአከባቢዎች ትምህርት መቀጠል የማይታሰብ በመሆኑ ወደ ጎንደር ከተማ በመሄድ ለመመዝገብ እና ትምህርት ለመቀጠል እንዳሰበ አስረድቷል።

በምስራቅ ጎጃም ዞን ጎንቻ ቀበሌ ተማሪ የነበረው ደሳለኝ በበኩሉ በአከባቢው ባለው ከፍተኛ የጸጥታ ችግር የተነሳ ትምህርቱን ለማቋረጥና በግብርና ስራ ላይ ለመሰማራት መገደዱን ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግሯል።

“አሁን ላይ በአከባቢያችን ትምህርት የለም። ምዝገባዎችም እየተካሄዱ ያሉት በከተሞች እና ኮማንድ ፖስት ባለባቸው አከባቢዎች ብቻ ነው። እኛ ትምህርታችንን አቋርጠን ወደ ግብርና ስራ ተቀላቅለን እየሰራን ነው” ሲል ደሳለኝ ገልጿል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2017 ዓ.ም. 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ ቢያቅድም እስካሁን የተመዘገቡት ከ2 ሚሊዮን እንደማይበልጡ ገልጿል።

የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው፤ እድሜያቸው ከ4 እስከ 6 ዓመት የሆናቸውን አንድ ሚሊዮን 760 ህፃናትን ለመመዝገብ ታቅዶ የተመዘገቡት 324 ሺህ ያክሉ ብቻ መሆናቸው ዶቼ ቬለ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከ1ኛ ክፍል እስከ 8ኛ ክፍል 4 ሚሊዮን 800ሺህ ተማሪዎች ይመዘገባሉ ቢባልም ባለፉት 20 ቀናት የተመዘገቡት ግን ከ1 ሚሊዮን 300ሺህ እንደማይበልጡ ሃላፊው አክለው ገልጸዋል።

በሁለተኛ ደራጅ ትምህርት ቤት 1 ሚሊዮን 200 ሺህ ተማሪዎች ለመመዝገብ ቢታቀድም እስከአሁን መመዝገብ የተቻለው ግን 300ሺህ ያክሉን ብቻ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።

የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆን በዋነኝነት በክልሉ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ መንሰኤ መሆኑን ገልጸው ከዚህ በተጨማሪ የተማሪዎች ዘግይቶ የመመዝገብ ልማድ፣ ፖለቲካን ከትምህርት ጋር የማያያዝ ጉዳዮችና ሌሎች ምክንያቶችን አንስተዋል።

“ትምህርት ከየትኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ጋር የማይገናኝ ነው።” ያሉት ሃላፊው አክለውም “በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች የመማር ማስተማር ሥራውን ከማደናቀፍ ሊታቀቡ ይገባል” ብለዋል፡፡አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button