ትንታኔፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ትንታኔ: በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ውስጥ ግብፅ እጇን ለምን አስገባች?

በአብዲ ቢያንሳ @ABiyenssa

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15/ 2017 ዓ/ም፦ በታህሳስ ወር 2016 ዓ.ም. በአፍሪካ ቀንድ በርካታ ውጥረቶችን ያስከተለ ዋነኛ ክስተት ተፈጠረ። ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ መሠረት ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ዕውቅናን ለመስጠት፣ ሶማሊላንድ ደግሞ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ለመፍቀድ መስማማታቸውን ተከትሎ በቀጠናው የፖለቲካ ምኅዳር ላይ ጉልህ ለውጥ እየተስተዋለ ይገኛል። 

ሶማሊያ ስምምነቱን ወዲያው ተቃውማለች። በሞቃዲሾ የሚገኘው የሶማሊያ ፌደራል መንግስት ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ በሶማሌላንድ ላይ ምንም አይነት ስልጣን ባይኖረውም የመግባቢያ ሰነዱን “ህገወጥ” በማለት ኢትዮጵያ የ”ሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እየጣሰች ነው” ሲል ከሷል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሁለቱ ሀገራት መካከል ውጥረት የነገሰ ሲሆን፤ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሀሙድ የሃገራቸውን ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ አቅም ለማጠናከር በማለም ከግብፅ ጋር የተፈራረሙት ወታደራዊ ስምምነት ሐምሌ 12 ቀን 2016 ዓ.ም. በሶማሊያ ካቢኔ ፀድቋል

ከአንድ ወር በኋላ በነሐሴ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ሁለት የግብፅ ወታደራዊ አውሮፕላኖች መሳሪያ እና ጥይቶችን ጭነው ሞቃዲሾ አውሮፕላን ማረፊያ መድረሳቸውን ሮይተርስ ዘግቧል። በተጨማሪም ግብፅ በሚቀጥለው አመት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ አካል የሚሆኑ 10,000 ወታደሮችን ወደ ሶማሊያ ለመላክ በዝግጅት ላይ መሆኗ ተዘግቧል። ይህ እርምጃም ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ውጥረት የበለጠ በማባባስ ግጭት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

ጳጉሜ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. የተከበረውን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ቀንን አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፣ “ ማንም ኢትዮጵያን መድፈር ሲፈልግ አንዴ ብቻ ሳይሆን አሥር ጊዜ ማሰብ ይኖርበታል” ሲሉ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

የአለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት ኢያሱ ኃይለሚካኤል ቀጥተኛ ወታደራዊ ግጭት የመፈጠሩ ስጋት ዝቅተኛ ቢሆንም በግብፅ በምትደገፈዋ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መካከል ቀጥተኛ ያልሆነ ግጭት የመፈጠር ዕድሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው ይህም ጉልህ የሆነ ቀጠናዊ አንድምታ እንዳለው ጠቁመዋል። 

እንደ ኢያሱ ገለጻ፣ የአፍሪካ ቀንድ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ፣ በተለይም ለአለም አቀፍ ንግድ ወሳኝ የባህር ኮሪደር ለሆነው ለቀይ ባህር ያለው ቅርበት ቀጠናዊ መረጋጋትን ወሳኝ ያደርገዋል ያሉ ሲሆን፣ እየተፈጠረ ያለው አለመግባባት የአቅርቦት ሰንሰለቶችን በማወክ እና የኢኮኖሚ ልማትን በማደናቀፍ ቀድሞውኑ ደካማ የሆነውን አካባቢ ለበለጠ አለመረጋጋት ሊዳርገው ይችላል ሲሉ ገልጸዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

አቶ ኢያሱ አክለውም እንደ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያ እና የባህረ ሰላጤው የትብብር ምክር ቤት ያሉ የውጭ ኃይሎች ተሳትፎ ሁኔታውን ያወሳስበዋል ያሉ ሲሆን፣ ይህም “የአፍሪካ ቀንድ የቀጠናዊ ጦርነት አውድማ እንዳይሆን ስጋት ፈጥሯል” ሲሉ ተናግረዋል። 

የግብፅ ተሳትፎ፡ እውነተኛ ድጋፍ ወይስ ስልታዊ እንቅስቃሴ?

የሃይድሮ ፖለቲክስ ተመራማሪው አስራት ብርሃኑ የግብፅ ተሳትፎ በትንሹ ሶማሊያን ለመደገፍ ያለመ ሲሆን በዋናነት ግን ኢትዮጵያ በቀጠናው ላይ ያላትን ተጽእኖ በመመከት ላይ ያተኮረ ነው ይላሉ።

በተጨማሪም ግብፅ ከሶማሊያ ጋር ያላትን ወታደራዊ ትብብር፤ ከኢትዮጵያ በተቃራኒ ቀጠና ለመፍጠር እና  በዓባይ ወንዝ ውዝግብ ውስጥ የበላይነት ለማግኘትና የራሷን ጥቅም ለማስጠበቅ እየተጠቀመችበት ነው ሲሉ ጠቁመዋል።

ተመራማሪው አክለውም ከሶማሊያ ጋር የተደረገው ወታደራዊ ስምምነት ሀገሪቱን በ”ግብፅ ተፅዕኖ ስር ለመክተት የተደረገ ሙከራ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። 

ይህ የግብፅ ስትራቴጂ “የሶማሊያን ሉዓላዊነትና መረጋጋት በመናድ እንዲሁም የውስጥ ክፍፍልን በማባባስ ቀጣናውን የበለጠ ሊያናጋ ይችላል።” ሲሉም ተናግረዋል። 

በአሜሪካ የሰላም ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት ሙስጠፋ አሕመድ በበኩላቸው፤ የግብፅ ተቀዳሚ ፍላጎት በሶማሊያ ጸጥታ እና ደኅንነት ውስጥ ገንቢ ሚና ከመጫወት ይልቅ ኢትዮጵያን ማግለል እንደሆነ ጠቁመዋል።

“የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር አለመሳካቱ እና ኢትዮጵያ በግድቡ የውሃ ሙሌትን መቀጠሏ በካይሮ ላይ ከፍተኛ የውስጥ ጫና አሳድሯል” ያሉት ተመራማሪው በተጨማሪም “ግብፅ የኢትዮጵያ የባህር ኃይል በቀይ ባሕር ላይ መገኘትን ለመቀበል ፈቃደኛ አይደለችም” ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

ተመራማሪው ሶማሊያ ከግብጽ ጋር እያደረገች የምትገኘው ወታደራዊ ትብብር የቀጠናውን የውስጥ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ያወሳስበዋል ሲሉ ይሞግታሉ።

አንዳንድ የሶማሊያ ፌዴራል ግዛቶች ግብፅ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ (አውሶምን) ውስጥ በመሳተፏ ደስተኛ እንዳልሆኑ በመግለጽ፤ የሞቃዲሾ መንግስት ከአገሪቱ ማስወጣት የሚፈልገውን የኢትዮጵያ ጦር እንዳይወጣ አሳስበዋል።

በቀይ ባህር ቀጠና ጉዳይ ላይ ስፔሻላይዝ ያደረጉት የትሪስቴ ዩኒቨርሲቲ የአለም አቀፍ ግንኙነት ፕሮፌሰር ፌዴሪኮ ዶኔሊ በበኩላቸው ግብፅ በሶማሊያ የምታደርገው እንቅስቃሴ በ”ዕቅድ” እና በ”እድል የሚመራ” እንደሆነ ያብራራሉ።

“ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ስልታዊ በሆነ መልኩ በተለይም በዲፕሎማሲ ስራ የግብፅን ቀጣናዊ ተፅእኖ ለማደስ በመስራት ላይ ይገኛሉ” ያሉት ፕሮፌሰሩ በተመሳሳይ “ሶማሊያ ለግብፅ ያቀረበችው የዕርዳታ ጥያቄ፤ በሁለቱ አገሮች (በኢትዮጵያ እና በግብፅ) መካከል ያለው ፉክክር እየጨመረ ባለበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያን ለመግታት ዕድል ይሰጣታል” ሲሉ ገልጸዋል።

ነገር ግን ከሌሎች ቀጠናዊ ኃይሎች ሊመጣ የሚችለው ምላሽ እና ውስብስብ ውስጣዊ ሁኔታዎች ከሶማሊያ አስቸጋሪ የመሬት አቀማመጥ ጋር ተዳምረው “የግብፅ ወታደሮች ከገመቱት በላይ የበለጠ ተጋላጭነት ሊያጋጥማቸው ይችላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ፌዴሪኮ አክለውም የግብፅ እንቅስቃሴ ቀጠናዊ የሃይል ሚዛኑን ሊቀይር እና አዳዲስ የሃይል አሰላለፎችን ሊፈጥር ይችላል ሲሉ አመላክተዋል።

ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔዎችን ማሰስ

ቱርክ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን ለማሸማገል በአንካራ ሁለት ዙር ንግግሮችን በማመቻቸትጥረት አድርጋለች። መጀመሪያ ላይ እነዚህ ውይይቶች ለችግሩ መፍትሄ የሚሆን የተስፋ ጭላንጭል ቢሰጡም ሊታረቁ በማይችሉ ልዩነቶች ምክንያት ሳይሳኩ ቀርተዋል።

ሶማሊያ ኢትዮጵያ የመግባቢያ ሰነዱን እንድታፈርስ ስትጠይቅ በአንፃሩ ኢትዮጵያ የባህር ላይ ተደራሽነትን “በጋራ የስምምነት ማዕቀፍ ” ውስጥ ለመተግበር ትፈልጋለች።

ምንም እንኳን ባለሙያዎች የመሳካት ዕድሉ ላይ ጥርጣሬ ቢኖራቸውም ሦስተኛው ዙር ንግግር ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለታል።

በቱርክ የአፍሪቃ ፖሊሲ ፀሃፊ ፌዴሪኮ ዶኔሊ፣ “ቱርክ ሁለቱን ሃገራት ለማሸማገል ጥረት ብታደርግም ያሉት መሰረታዊ ጉዳዮች በጣም ውስብስብ ናቸው” ሲሉ ጠቁመዋል።

“ኢትዮጵያ በቀይ ባህር የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ታቋርጣለች ብሎ ማሰብና ከባድ ነው፤ ሶማሊያም ከሶማሌላንድ ጋር የተደረሰውን የመግባቢያ ስምምነት ትቀበላለች ማለት ማለት አዳጋች ነው” ብለዋል።

ፌዴሪኮ፤ “ከአንደኛው ወገን የሚመጣ መለሳለስ ብቻ ነው ይህን ውዝግብ ሊገታ የሚችለው፣ ይህን ደግሞ ሁለቱም ሀገራት ለመፈፀም ፈቃደኛ አይመስሉኝም” ሲሉ ገልጸዋል።

ሙስጠፋ አህመድ በበኩላቸው የሶማሌላንድ ዓለም አቀፍ እውቅና ለማግኘት የምታደርገው ጥረት ዋናው ጉዳይ መሆኑን ይገልጻሉ። “ሶማሊያ የሶማሊላንድን ነፃነት የሚመለከቱ ስምምነቶችን መቃወሟን ትቀጥላለች፤ ነገር ግን የመግባቢያ ሰነዱ ይህንን ችግር መፍታት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁሟል” ብለዋል።

ሶማሊያ ከግብፅ ጋር የፈጠረችው ወታደራዊ ትብብር፣ የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲ በማወሳሰብ የቱርክ የአሸማጋይነት ጥረት ላይ እንቅፋት እቅፋት ሊፈጥር ይችላል ይላሉ።

ኢያሱ ኃይለሚካኤልም በበኩላቸው በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ያለው ሥር የሰደደ አለመተማመን፣ ከታሪካዊ ውጥረቶች ጋራ ተዳምሮ መግባባትን እጅግ አስቸጋሪ ያደርገዋል ባይ ናቸው። አክለውም “ይህ አለመተማመን እስካሁን በተደረጉት የንግግር ሂደቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።

ውጥረቱ እየተባባሰ በሄደ ቁጥር የዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ አስፈላጊነት ይጨምራል ያሉት ኢያሱ እንደ አፍሪካ ህብረት ወይም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በመሳሰሉ ገለልተኛ አካላት የሚመቻች ዘላቂ አህጉራዊ ውይይት ውጥረቱን ለማርገብ እና በቀጠናው ዘላቂ መረጋጋትን ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button