ዜናፖለቲካ

ዜና: በደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው የህወሓት ቡድን በጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ “መፈንቅለ ስልጣን ሊያካሂድ በማቀድ ላይ ይገኛል” ሲል የአቶ ጌታቸው ቡድን ኮነነ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9/2017 ዓ.ም፡- በአቶ ጌታቸው ረዳን የሚመራው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትና ከፍተኛ አመራሮች ትላንት መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጡት መግለጫ በደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው የህወሓት ቡድን በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ላይ “መፈንቅለ ስልጣን ለማካሄድ ማቀዱን” በግልጽ እያስታወቀ ይገኛል ሲል ኮነነ።

“ለራሱ ምንም አይነት ህጋዊነት የሌለው ቡድን በክልሉ በሚገኝ የትኛውም ተቋም ላይ ምንም አይነት እርምጃ መውሰድ አይችልም፤ ሞራላዊ፣ ፖለቲካዊ መሰረትና ቅቡልነት የሌለው ቡድን መሆኑን ልንገልጽ እንወዳለን” ሲል አስታውቋል።

“የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ይህ ህገ ወጥ ቡድን ህግና ስርዓት እየጣሰ እንዲቀጥል መፍቀድ የለበትም፤ ስርአት ያስይዝልን” ሲል ጠይቋል።

በነሃሴ ወር 2016 ዓ.ም መጀመሪያ ሰሞን በመቀለ ከተማ በሐውልቲ አዳራሽ 14ኛ ጉባኤውን ያካሄደው የህወሓት ቡድን ደብረጺዮን ገ/ሚካኤልን ሊቀመንበር አድርጎ መምረጡ ይታወሳል።

በደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መስከረም 5 ቀን 2017 ዓ.ም አካሄድኩት ባለው የማዕከላዊ ኮሜቴ ስብሰባ ምክትል ሊቀመንበሩ የነበሩትን አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 16 ነባር አባላቱን እና ከፍተኛ አመራሮቹን ማገዱን ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።

16ቱ ከፍተኛ አመራሮቹ ህወሓትን ወክለው ምንም አይነት የፖለቲካዊ ውስኔ መፈጸም አይችሉም ብሏል።

በሓውልቲ አዳራሽ በተካሄደው የህወሓት ጉባኤ ያልተሳተፈው እና በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የህወሓት ቡድን ትላንት መስከረም 8 ቀን ባወጣው መግለጫ የእነደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ቡድን የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር መዋቅር በማፍረስ “ትግራይን መንግስት አልባ ለማድረግ እና የግርግርና ቀውስ ማዕከል ለማድረግ እየሰራ ነው” ሲል ኮንኗል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የአቶ ጌታቸው ረዳ ቡድን በመግለጫው “የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት በአግባቡ እንዲከበር በመታገል ላይ እንገኛለን ሲል ገልጾ በደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ቡድን “የክልሉ ህዝብ በመስዋዕትነት ያመጣውን ድል አደጋ ውስጥ የሚከት እንቅስቃሴ እያደረገ ነው” ሲል ተችቷል። “መላ የክልሉ ህዝብ እና የፓርቲው አባላት ይህንን ለስልጣኑ ሲል በተደጋጋሚ የክልሉን ህዝብ ዋጋ ያስከፈለ የጥፋት ቡድን ሊታገለው ይገባል” ሲል አሳስቧል።

ጉባኤ ያካሄደው ቡድን “አሁንም በስህተት ሌላ ስህተት እየሰራ የትግራይን ህዝብ ወደ አላስፈላጊ ትርምስ ውስጥ እያስገባው ነው፣ በህዝባችን ላይ ተደጋጋሚ ክህደት እየፈጸመ ነው” ሲል በመግለጫው የኮነነው የአቶ ጌታቸው ቡድን በቅርቡ “በሆራይዘን ሚዲያ ቀርበው” ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የሰጡትን አስተያየት በማሳያነት አስቀምጧል።

ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) በሚዲያው ቀርበው በሰጡት አስተያየት “በትግራይ በተካሄደው ጦርነቱ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ አልቋል የሚባለው ነገር በጥናት ላይ ያልተመሠረተና ማስረጃ የሌለው፣ አመራሩን ተጠያቂ ለማድረግ ሲባል ብቻ የሚነገር ነገር እንደኾነ” ገልጸዋል።

ዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል ይህንን አስተባብለው በይፋዊ የማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ “ከቁጥር ጋር የተያያዘ ውዥንብር እንደፈጠረ መረዳታቸውን” ገልጸው እንዲያውመ ከዚህም ሊልቅ ይችላል ብለዋል።

የአቶ ጌታቸው ቡድን በመግለጫው ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) አስተያየት “በትግራይ ህዝብ ለደረሰው የዘር ማጥፋት ፍትህና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ከመታገል ይልቅ የዘር ማጥፋት ተግባሩን የቁጥር ጨዋታ በማድረግ የትግራይ ወጣቶችን ትግል፣ መስዋዕትነት እና ጉዳት አሳንሷል” ሲል ኮንኗል።

“በትግራይ የተፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል መሰረተ ቢስ፣ ማስረጃ የሌለው እና ለስልጣን ተብሎ የተፈበረከ ነው” ሲሉ ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል ተናግረዋል ሲል ገልጿል።

“ይህ ጉዳይ እንደ ተራ ስህተት ችላ ሊባል አይችልም” ያለው የአቶ ጌታቸው ቡድን “የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል የመካድ ከባድ ወንጀል መሆኑን ይታወቅልን ብሏል።

የደብረጺዮን ቡድን “የተጭበረበሩ ሃሳቦቹን ለመሸፈን እና አጀንዳውን ለማስቀየስ መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ማቀዱን በግልፅ አስታውቋል” ብሏል።

የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር እና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 17 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የድርጅቱ ቁጥጥር ኮሚሽን፣ አብዛኞቹ የደቡብ እና የደቡብ ምሥራቅ ትግራይ ወረዳዎች እንዲሁም የመቀለ ከተማ ክፍለ ከተሞች በሓወልቲ አደራሽ በተካሄደው ጉባኤ ሳይገኙ መቅረታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በከፍተኛ አመራሮቹ ክፍፍል መካከል በተደረገው በ14ኛው የህወሓት ጉባኤ ያልተገኙ እና በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ያሉ “የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና ስራ አስፈጻሚዎች ድርጅቱን እንደማይወክሉ” የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ማስታወቃቸውም በዘገባው ተካቷል።

በሌላ በኩል በሐወልቲ ሰማእታት አደራሽ በተካሄደው የህወሓት ጉባኤ “የሚተላለፉ ውሳኔዎች ተቀባይነት የላቸውም” ሲል በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ቡድን ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን መዘገባችንም ይታወሳል።

በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ውስጥ ያሉ ሁለቱም ቡድኖች በክልሉ የሚታየውን ፖለቲካ ሁኔታ ወደ ቀውስ የሚከት እና በህዝቡ ዘንድ መከፋፈልን ከሚፈጥሩ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች እንዲታቀቡ ሲሉ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት እና የሰላምና ጸጥታ ሴክሬተሪያት ሃላፊ ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ማስጠንቀቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button