ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ በምስራቅ ጎጃም ዞን አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት በተፈጠረባቸው ወረዳዎች ትምህርት መጀመሩ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24/2016 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል በምስራቅ ጎጃም ዞን በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የ2016 የትምህርት ዘመን በወቅቱ ያልተጀመረ ቢሆንም የተሻለ ሰላምና መረጋጋት ካለባቸው ወረዳዎች መካከል በደጀን ወረዳ አስተዳደር በሚገኙ አምስት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ስራው በይፋ መጀመሩን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታውቋል።

አጠቃላይ የመማር ማስተማር ስራውንም የዞኑ አመራሮች በወረዳው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተዘዋውረው ምልከታ ማድረጋቸውን በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ የጠቆመው የክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ መምህራንና የትምህርት አመራሮች የመማር ማስተማሩን ተግባር በተደራጀ መንገድ እየፈጸሙ መሆኑንም አረጋግጠዋል ብሏል።

ይህንን ተግባር ወደሌሎች ወረዳዎችእና ቀሪ ትምህርት ቤቶች ለማስፋት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ያመላከተው የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን መረጃ በቅርቡ ተጨማሪ አምስት ወረዳዎች የመማር ማስተማር ስራቸውን ማከናወን የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራቸውን ማጠናቀቃቸውን የመምሪያ ኃላፊው አቶ ጌታሁን ፈንቴ ገልጸዋል ብሏል።

በበጀት ዓመቱ እንደ ዞን ከቅድመ አንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ633,000 በላይ ተማሪዎችን ለማስተማር በእቅድ ተይዞ እየተሰራ ቢሆንም በዞናችን የተፈጠረው የሰላም እጦት የትምህርት ስራውን ከመጉዳቱም በላይ በተለይም ክልልና ሃገርአቀፍ ፈተና በሚወስዱ ተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል ማለታቸውንም መረጃው አካቷል።

ይህንን ጫና ለመቀነስና ለመፍታት ከሚመለከታቸው አጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ሃላፊው መግለጻቸውን እና ወላጆችና መላ ህዝባችን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ እና ትምህርታቸውን ያለስጋት እንዲከታተሉ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ ሲል ጥሪ ማስተላለፉን አስታውቋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button