ቢዝነስዜና

ዜና፡ በሩብ አመቱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከ249 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 20/2016 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የሚያስተዳድራቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በሩብ ዓመቱ ከ249 ቢሊየን ብር ብላይ ገቢ ማግኘታቸው ተገለጸ።

በ2016 በጀት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የልማት ድርጅቶች የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ያስሚን ወሀብረቢ መናገራቸውን ያስነበበው ኢዜአ ድርጅቶቹን በዓለም አቀፍ የትርፋማ ቢዝነስ ሞዴል እንዲመሩ ሰፊ የለውጥ ሥራዎች በመከናወናቸው ወደ ከፍተኛ ትርፋማነት ተሻግረዋል ሲሉ መግለጻቸውን አስታውቋል።

ለአብነትም በ2015 በጀት አመት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ከ924 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ሃላፊዋ አውስተዋል ያለው ዘጋው ከዚህም ከታክስ በፊት 118 ቢሊየን ብር ትርፍ አስመዝግበዋል ማለታቸውን አካቷል።

በ2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ደግሞ 249 ቢሊየን ብር ገቢ ከልማት ድርጅቶች መገኘቱን ያነሱት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት የ43 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን እና ከታክስ በፊት 35 ቢሊየን ብር ትርፍ ማስመዝገባቸውን መናገራቸውን አመላክቷል።

በሩብ ዓመቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ-ቴሌኮም፣ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የላቀ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ድርጅቶች መሆናቸውን ዘገባው ጠቅሷል።

በሌላ በኩል የስኳር ፋብሪካዎች፣ ፐልፕና ወረቀት እንዲሁም የማዕድን ኮርፖሬሽን አሁንም በኪሳራ ላይ መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው ሆኖም የኪሳራ መጠናቸው ከዓመት ወደ ዓመት እየቀነሰ መምጣቱን ሃላፊዋ መግለጻቸውን አስታውቋል።

የስኳር ፋብሪካዎች በ2014 በጀት ዓመት ያስመዘገቡት ኪሳራ 5 ቢሊየን ብር እንደነበር አስታውሰው፤ በ2015 በጀት ዓመት ግን ወደ ግማሽ ቢሊየን ማውረድ ተችሏል ሲሉ በአብነት መጥቀሳቸውን አካቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

እነዚህን ድርጅቶች ሙሉ ለሙሉ ከዕዳ በማላቀቅ ወደ ትርፋማነት ለማሸጋገር የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ቦርድ የኩባንያ የሽግግር ፕሮግራም ማጽደቁን ጠቁሟል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button