ቢዝነስዜና

ዜና፡ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ያለው የቁጠባ ገንዘብ መጠን ከ2 ትሪሊዮን ብር በላይ ማለፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26/2016 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ያለው የቁጠባ ገንዘብ መጠን ከ2 ትሪሊዮን ብር በላይ ማለፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ። የህብረተሰቡ የቁጠባ ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻልና ለውጥ እየታየበት ይገኛል ሲሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ ሰለሞን ደስታ መናገራቸውን ያስታወቀው የኢዜአ ዘገባ በመሆኑም ባንኮችን ጨምሮ በተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት አጠቃላይ የቁጠባ ገንዘብ መጠን 2 ነጥብ 19 ትሪሊዮን ብር ደርሷል ማለታቸውን ጠቁሟል።

የቁጠባ መጠኑ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በ25 በመቶ እድገት ማሳየቱንም ተናግረዋል ያለው ዘገባው የዲጂታል ፋይናንስ ስርዓትን በተለያዩ አማራጮች ለሕብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ የቁጠባና የፋይናንስ እንቅስቃሴ እንዲሳለጥ ተደርጓልም ማለታቸውን አስታውቋል።

የዲጂታል ስርዓቱ መስፋፋት፣ የአዳዲስ ባንኮች ወደ ስራ መግባት፣ የካፒታል ገበያና የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ የመግባት እድል ተዳምረው ለቁጠባ ማደግ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆኑ ገልጸዋል ያለው ዘገባው የፋይናንስ ዘርፉን ጨምሮ በሁሉም መስኮች የዲጅታል ቴክኖሎጂን ተግባራዊ በማድረግ በ2025 ዓ.ም ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እየተሰራ ነው ማለታቸውን አመላክቷል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button