ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ ጃል ማሮ የተካፈለበት በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እና በፌደራል መንግስቱ መካከል በዳሬሰላም ሁለተኛው ዙር የሰላም ውይይት ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28/2016 ዓ.ም፡- በፌደራል መንግስቱ እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል በታንዛንያ ዳሬሰላም ሁለተኛው ዙር የሰላም ውይይት ትላንት ጥቅምት 27 ቀን 2016 ዓ.ም መጀመሩን ጉዳዩን ከሚከታተሉ ሁለት ዲፕሎማቶች አዲስ ስታንዳርድ አረጋግጣለች።

በሰላም ውይይቱ ላይ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መሪ ኩምሳ ደሪባ በቅጽል ስሙ ጃል ማሮ በመሳተፍ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቁት ጃል ማሮ በሶስተኛ ወገን አደራዳሪዎች አመቻችነት በምዕራብ ኦሮምያ ከሚገኝ ጫካ ወደ አቅራቢያው ወደሚገኘው የደንቢዶሎ አየር ማረፊያ እንዲበር መደረጉን ጠቁመው ከዚያም ወደ ድርድሩ ቦታ በተዘጋጀለት ሄሎኮፕተር መጓዙን ተናግረዋል። በዚህም ሂደት ጃል ማሮ ለመጀመሪያ ግዜ ከፌደራል መንግስቱ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ጋር ፊት ለፊት ለመገናኘት መቻሉንም አመላክተዋል።

አዲስ ስታንዳርድ ከምንጮቻ እንደተረዳችው ከሆነ ባሳለፍናቸው ሶስት ሳምንታት የፌደራል መንግስት እና የኦሮምያ ክልል መንግስት ከፍተኛ ሃለፊዎች እንዲሁም ሁለት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አመራሮች ተሳታፊ የሆኑበት ውጤታማ የተባለ የፖለቲካ ውይይቱ ተካሂዷል።

ውይይቱ ውጤታማ ስለነበር እና በዚህም ምክንያት የፌደራል መንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች የተሳተፉበት ውይይት ትላንት ጥቅምት 27 ቀን 2016 ዓ.ም መጀመሩን ምንጮቻችን ገልጸዋል።  

ከሁለቱም ወገን ከሳምንታት በፊት በተካሄደው በቀደመው የፖለቲካ ውይይት ተካፋይ የነበሩ ከፍተኛ አመራሮች ድርድሩ በስኬት ከተከናወነ ለፊርማ ስነስርአቱ ተካፋይ እንደሚሆኑ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የዲፕሎማቲክ ምንጮቻችን ጠቁመዋል።

ውይይቱን በማመቻቸት ረገድ ኢጋድ ትልቁን ሚና መጫወቱን የጠቆሙት ምንጮች የኢጋዱ ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ዋና አወያይ መሆናቸውንም ዲፕሎማቲክ ምንጮቻችን አስታውቀዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ሚያዚያ 15 ቀን 2015 ዓ.ም የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንዲያበቃ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት በተዘጋጀ የሽልማት እና የእውቅና መርሃ ግብር ላይ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ባደረጉት ንግግር መንግስት ከ“ኦነግ ሸኔ” ጋር በዛንዚባር ከሚያዚያ 17 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ድርድር እንደሚያደርጉ ማስታወቃቸውን ተከትሎ የመጀመሪያው የድርድሩ ሂደት መጀመሩ ይታወሳል።

ጠ/ሚንስትር አብይ ከኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ጋር በታንዛኒያ ድርድር እንደሚጀመር መግለፃቸውን ተከትሎ ቡድኑ ባወጣው መግለጫ መንግስት ሶስተኛ አካል ባለበት ድርድር ለማድርግ የቀረቡ ቅድመ ሁኔታዎችን በመቀበሉ ድርድሩ እንደሚጀመር ማረጋገጡ በዘገባው ተካቷል፡፡

በመንግስትና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መካከል በታንዛኒያ የተካሄደው ድርድር ሳምንት ያክል ከፈጀ በኋላ ከስምምነት ላይ መድረስ አለመቻሉን መንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በየፊናቸው ባወጡት መግለጫ ማስታወቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በወቅቱ በመንግስት በኩል የሰላም ድርድሩ የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቀቀ በሚል የተገለጸ ሲሆን ውይይቱ በአብዛኛው በአዎንታዊ መልኩ መከናወኑን በመግለጽ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ግን በዚህኛው የውይይት ምዕራፍ ስምምነት ላይ ለመድረስ አልተቻለም ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ አመላክቷል፡፡ ግጭቱን በዘላቂነትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማስቆም እንዲቻል ሁለቱም አካላት የሰላም ውይይቱን መቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ላይ ተግባብተዋል ብሏል መግለጫው።

የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በበኩሉ ባወጣው ምግለጫ የመጀመሪያው የድርድሩ ምዕራፍ መጠናቀቁን ገልፆ በወሳኝ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ላይ አለመደረሱን አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከመግባባት ላይ መደረሱን ገልጧል፡፡

ሁለቱም ተደራዳሪ አካላት በቀጣይ ተገኛኝተው ውይይቱን በማስቀጠል በሰላማዊ መንገድ በዘላቂነት ግጭትን ለመፍታት መስማማታቸውን አስታውቋል፡፡ አክሎም አሁንም ግጭትን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ገልጧል፡፡ በመጨረሻም ውይይቱ እNዲካሄድ ላመቻቹ አካላት ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

በታንዛኒያ ዛንዚባር ሲከናወን የቆየውን የድርድር መድረክ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የፍትህ ሚንስትሩ ዶ.ር ጌዲዮን ጢሞትዎስ፣  የኦሮሚያ ክልል የፍትህ እና ደህንነት ክላስተር በምክትል ሃላፊ ከፍያለው ተፈራ፣ በመከላከያ ሰራዊት ወታደራዊ መረጃ ምክትል ሀላፊ ሜጀር ጀነራል ደምሰው አመኑ፣ ቦንሳ እውነቱ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና በታንዛኒያ የኢትዮጳያ አምባሳደር ሽብሩ ማሞ መወከላቸውን አዲስ ስታንዳርድ ዘግባለች፡፡ በኦሮሞ በፃነት ሰራዊት በኩል ደግሞ ካረጋገጥናቸው ተሳታፊዎች መካከል ፕሮፌሰር መሀመድ ሀሰን፣ ጣሃ አብዲ፣ ዶ/ር ባንቲ ኡጁሉ እና ኤጄርሶ ኡርጌሳ ከተሳታፊዎች መካከል መሆናቸውን አዲስ ስታንዳርድ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button