ዜናፖለቲካ

ዜና: የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ የአፍሪካን እውነተኛ ውክልና ባረጋገጥ መልኩ እንዲከናወን ኢትዮጵያ ጠየቀች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13/2017 ዓ.ም፡- በኒውዮርክ እየተካሄደ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 79ኛው ጠቅላላ ጉባዔ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሤ ባሰሙት ንግግር የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ የአፍሪካን እውነተኛ ውክልና ባረጋገጥ መልኩ እንዲከናወን ጠይቀዋል።

አምባሳደር ታዬ ከአልጀሪያ እና ከደቡብ ሱዳን አቻዎቻቸው ጋርም በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸው ታውቋል።

አምባሳደር ታዬ ምክር ቤቱን ለማሻሻል የሚደረገው እንቅስቃሴ የአፍሪካን የውክልና አድማስ ከሁሉም መመዘኛዎች አንጻር ታሳቢ ሊያደርግ እንደሚገባው መጠየቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ሚኒስትሩ አገራት ድህነትን ለማጥፋት የሚያደርጉት ጥረት በራሳቸው የፖሊሲ ማዕቀፍ ምርጫ አግባብ የተጠናከር ድጋፍ እንዲደረግላቸው እና ለጉዳዩ ቀዳሚ ትኩረት እና የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንዲኖር ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ በጉባዔው የፀደቁት ሠነዶች Pact for the Future, Declaration on Future Generations, Global Digital Compact የድርድር ሂደት ላይ ተሳትፎ ስታደርግ ቆይታለች።

የሠነዱ መፅደቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ድህነት፣ ረሃብ፣ የአየር ንብረት ቀውስ፣ አደገኛ ግጭቶች፣ ወረርሽኞች እና ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር ተያይዘው የሚመጡ አደጋዎች እያደጉ በሚገኙበት ወቅት፣ የጋራ ምላሽ እና መፍትሄ ለመስጠት ዕድል እንደሚፈጥር ታምኖበታል።

የዋና ፀሐፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ኢኒሼቲቭ የሆነውና ከ140 በላይ የአገር መሪዎች የሚሳተፉበት የመጪው ጊዜ ጉባዔ (Summit of the Future) ተከፍቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በሌላ ዜና በኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው የተመድ 79ኛው ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከአልጀሪያ እና ከደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸው ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከአልጄሪያ አቻቸው አህመድ አታፍ ጋር ባካሄዱት ውይይት ኢትዮጵያና አልጄሪያ ረጅም ጊዜ የቆየ ጠንካራ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው አገራት መሆናቸውን በመጥቀስ ሁለቱ አገራት በተለይ በአፍሪካ አህጉር በሚታዩ የሠላምና ፀጥታ ጉዳዮች ይበልጥ ተቀናጅተው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መግለጫ ያሳያል።

ሚኒስትሮቹ በቅርቡ ለሚካሄደው አምስተኛው ኢትዮ -አልጄሪያ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ቅድመ ዝግጅት ያለበት ደረጃ ላይም ሃሳብ መለዋወጣቸውንም ጠቁሟል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ ከደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ከተከበሩ ራምዳን ሞሀመድ አብዱላህ ጋር በመነባረቸው ውይይት ሁለቱ አገራት በናይል ተፋሰስ ፍትሃዊ እና እኩል ተጠቃሚነት ላይ ባላቸው ወጥ አቋም ዙሪያ ሀሳብ መለዋወጣቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል።

አምባሳደር ታዬ፥ ደቡብ ሱዳን የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን በፓርላማ ማፅደቋን በማውሳት ራምዳን ሞሀመድ አብዱላህን እንኳን ደስ ያለዎት ብለዋቸዋል ያለው መረጃው የደቡብ ሱዳን ፓርላማ ስምምነቱን በማጽደቁ የአገሪቱ ሕዝብ በናይል ተፋሰስ በፍትሀዊነት እና እኩል ተጠቃሚነት ላይ ያለውን መብት ያስከበረ መሆኑን አምባሳደር ታዬ መግለጻቸውን አስታውቋል።

በውይይቱ ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ሙሉ ትግበራ በጋራ ለመንቀሳቀስ መስማማታቸውንም ጠቁሟል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button