ዜናፖለቲካ

ዜና: የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር “የክልሉ የጸጥታ አካላት በስሬ ሁነው እየተመሩ ይሰራሉ” ሲል አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13/2017 ዓ.ም፡- የትግራይ ክልል የጸጥታ አካላት በጊዜያዊ አስተዳደሩ እየተመሩ ይሰራሉ ሲል በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም አካሄድኩት ባለው መደበኛ ስብሰባ በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ በመምከር ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ይፋ አድርጓል፤ ከውሳኔዎቹ መካከልም በክልሉ የሚገኙ “የጸጥታ አካላት እንደ አንድ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አካል” መሆናቸውን ጠቁሟል።

“አግባብነት ባለው ጥናት እና ምክክር እየተደረገበት በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት እና በካቢኔው እየተመሩ በህግ እና በስርአት ተልዕኮ እየተሰጣቸው ይፈጽማሉ” ሲል አስታውቋል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ በመግለጫው የጸጥታ አካሉ “በማናቸውም የክልሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በሚፈጠር የትኛውም አጀንዳ ገለልተኛ አቋም ይዘው አንደሚሰሩ ልናረጋግጥ እንወዳለን” ብሏል።

በትግራይ ክልል የተፈጠረው ችግር በህወሓት እና በጊዜያዊ አስተዳደሩ መካከል ተደርጎ እየቀረበ ያለው ነገር ፍጹም የተሳሳተ እና የችግሩ ተወናዮች እንዲሁም አሰላለፋቸውን በሳተ መልኩ የቀረበ መሆኑን ህዝቡ በግልጽ ሊያውቅ ይገባል ብሏል።

ችግሩ በህወሓት የከፍተኛ አመራሮች መካከል የተፈጠረ ክፍፍል ነው ሲል ገልጿል።

የዚህ ችግር መዘዝ በመንግስት መዋቅር ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ቢሆንም እንደ ጊዜያዊ አስተዳደር እና እንደመንግስት እንዲሁም እንደመንግስት በሚያካሂዳቸው ስራዎችም ጋር በተያያዘ ሁኔታው የማይመለከተው መሆኑ ሊታወቅልኝ ይገባል ብሏል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሁሉም የክልሉ ህዝብ መንግስት ነው ሲል ገልጿል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ስራዎቹን እና እንቅስቃሴዎቹን ለማሳለጥ ይረዳው ዘንድ በተለያዩ እርከኖች የሚያካሂደውን የሃላፊነት ምደባ እንደሚቀጥልበትም አስታውቋል።

ይህ እንዳይካሄድ በማንኛውም መልኩ እንቅፋት በሚፈጥሩ አካላት ላይ በህጋዊ መንገድ መልክ ለማስያዝ እሰራሉ ሲል ገልጿል።

በተጨማሪም የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ “የማሳልፋቸውን ማናቸውንም ውሳኔዎቼን ለመሻርም ሆነ የመንግስትን መዋቅርን ለማወክ የሚደረግ ሙከራ ተቀባይነት የለውም” ብሏል።

ህወሓት በደብረጺዮን ገብረሚካኤል እና በአቶ ጌታቸው ረዳ በሚመሩት ሁለት ቡድን ተከፍሎ እየታመሰ እንደሚገኝ ከቅርብ ግዜያት ወዲህ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ያሳያሉ። ሁለቱም ቡድኖች በተለያዩ ግዜያት በየፊናቸው ባወጧቸው መግለጫዎች አንዱ አንዱ በመክሰስ ይወነጅላሉ።

በአቶ ጌታቸው ረዳን የሚመራው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትና ከፍተኛ አመራሮች መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጡት መግለጫ በደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው የህወሓት ቡድን በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ “መፈንቅለ ስልጣን ለማካሄድ ማቀዱን” በግልጽ እያስታወቀ ይገኛል ሲል መኮነኑን የተመለከተ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል።

በደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መስከረም 5 ቀን 2017 ዓ.ም አካሄድኩት ባለው የማዕከላዊ ኮሜቴ ስብሰባ ምክትል ሊቀመንበሩ የነበሩትን አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 16 ነባር አባላቱን እና ከፍተኛ አመራሮቹን ማገዱን ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል። 16ቱ ከፍተኛ አመራሮቹ ህወሓትን ወክለው ምንም አይነት የፖለቲካዊ ውስኔ መፈጸም አይችሉም ብሏል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button