ዜናፖለቲካህግ እና ፍትህ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በአማራ ክልል ከሐምሌ ወር ወዲህ በትንሹ 183 ሰዎች መገደላቸውን ተመድ አስታወቀ፤ በምዕራብ ትግራይ 250 የትግራይ ተወላጆች መታሰራቸውንም አመላክቷል

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 23/2015 ዓ.ም፡- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በአማራ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት ከሐምሌ ወር ወዲህ 183 ሰዎች መገደላቸውን አስታወቀ። በኢትዮጵያ በሚገኙ አንዳንድ ክልሎች እያሽቆለቆለ ያለው የሰብአዊ መብት ሁኔታ አሳስቦኛልም ብሏል።

በፋኖ ታጣቂዎች እና በሀገሪቱ መከላለከያ ሰራዊት መካከል የሚካሄደው ግጭት መጠናከሩ እና የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ መታወጁም ተጨምሮበት በአማራ ክልል ሁኔታዎች እጅጉን እየተባባሱ ነው ብሏል።

በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ለአስፈጻሚ ባለስልጣናቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ አዋጁን እንዲያስተገብሩ የተንቦራቀቀ ስልጣን ሰጥቷል ሲል የተቸው የመንግስታቱ ድርጅት ተጠርጣሪዎቹን በመላ ሀገሪቱ ተንቀሳቅሰው ለማሰር፣ ስአት እላፊ ለመጣል እና በርከት ብሎ መሰብሰብን ለመከልከል የተሰጣቸውን ስልጣን በአብነት ጠቅሷል።

በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ሳቢያ በመላ ኢትዮጵያ ከአንድ ሺ በላይ ሰዎች መታሰራቸውን የሚያሳይ ሪፖርት እንደደረሰውም አስታውቋል፤ አብዘሃኛዎቹም የአማራ ክልል ተወላጅ የሆኑ ወጣቶች መሆናቸውን እና ለእስር የዳረጋቸውም ፋኖን ትደግፋላችሁ በሚል መሆኑን ገልጿል።

ከነሃሴ ወር ወዲህ የቤት ለቤት ብርበራ እየተከናወነ መሆኑን የጠቆመው ተመድ በአማራ ክልል ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ሲዘግቡ የነበሩ ሶስት ጋዜጠኞች ለእስር መዳረጋቸውንም አመላክቷል። ታፍሰው የታሰሩትም ሰዎች መሰራተዊ ነገሮች ባልተሟሉባቸው ማጎሪያዎች ይገኛሉ ሲል ገልጿል።

መንግስት የጅምላ እስር እንዲያቆም፣ የመብት ገፈፋውም ቢሆን በህግ አግባብ እንዲሆን እና በጅምላ ለእስር የተዳረጉት እንዲፈቱ ጠይቋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ ሌሎች አካላት ታሳሪዎቹ ያሉበትን ሁኔታ ያለገደብ እንዲጎኙ መንግስት እንዲፈቅድ ጠይቋል። የፌደራል ሀይሎች የተወሰኑ የክልሉ ከተሞችን መቆጣጠራቸውን እና የፋኖ ታጣቂዎች ወደ ገጠሩ የክልሉ ክፍል ማፈግፈጋቸውን የተመለከቱ ሪፖረቶች መውጣታቸውን የጠቆመው ተመድ ሁሉም አካላት ግድያ እና መሰል ጥሰቶች እንዲቆሙ እና ችግሮቻቸውን በንግግር እና በፖለቲካ ሂደት እንዲፈቱ አሳስቧል።  

በሌላ ዜና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በምዕራብ ትግራይ በትንሹ 250 የሚደርሱ የትግራይ ተወላጆች በአዲስ መልክ በጅምላ መታሰራቸውን የሚያመላክት ክስ እንደደረሰው አስታውቋል። እስሩ የተፈጸመው በአማራ ፖሊስ፣ በአከባቢው ባለስለጣናት እና ሚሊሻ መሆኑን ያስታወቀው ተመድ እስሩ የተፈጸመውም የአማራ ሀይሎች በተቆጣጠሩት የምዕራብ ትግራይ ክፍል መሆኑን ገልጿል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button