ዜና

ዜና: ከአላማጣ ከተማ እና አከባቢዋ ተፈናቅለው ቆቦ እና ሰቆጣ የተጠለሉ ሰዎች ቁጥር 29 ሺ እንደሚጠጋ ተመድ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 12/2016 ዓ.ም፡- በቅርቡ በራያ አላማጣ አከባቢ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት ሳቢያ ከቀያቸው ተፈናቅለው በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ እና በዋግ ህምራ ዞን ሰቆጣ ከተማ ተጠልለው የሚገኙ ሰዎች ቁጥር 29 ሺ እንደሚጠጋ የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ቢሮ (ኦቻ) አስታወቀ።

አብዘሃኛዎ ህጻናት እና ሴቶች የሆኑ 23ሺ ተፈናቃዮች ቆቦ፣ 5ሺ 980 የሚሆኑት ደግሞ ሰቆጣ ከተማ ተጠልለዋል ያለው ቢሮው በአከባቢው ያለው ሁኔታ አሁንም የተረጋጋ ባለመሆኑ ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል ሚያዚያ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው ወቅታዊ ሪፖርት ጠቁሟል።

የምግብ እና ውሃ እጥረቱ አሳሳቢ ነው ያለው ቢሮው አፋጣኝ የነፍስ አድን እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቋል።

ሜዳ ላይ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃይ ቤተሰቦች በመኖራቸው ከለላ ሊሰጣቸው ይገባል ብሏል።

ቢሮው እና አጋር ተቋማት ያላቸው አቅርቦት ውስን በመሆኑ የአከባቢው ማህበረሰብ መደበኛ ባልሆነ መንገድ እጅግ ለተጎዱት የምግብ እና ውሃ ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሚገኝ ጠቁሟል።

ዘርፈ ብዙ እገዛ በአፋጣኝ ሊደረግላቸው እንደሚገባ የጠየቀው ቢሮው በተለይም መጠለያ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች እንዲሆን ጤናቸውን ለመጠበቅ የሚያስችላቸው እገዛ እንዲደረግላቸው አሳስቧል።

የኢትዮጵያ አደጋ እና ዝግጁነት ኮሚሽን ወደ ቦታው ሚያዚያ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ጉዳዩነ የሚከታተል ቡድን መላኩን አመላክቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button