ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: በራያ አላማጣ በተከሰተው ግጭት ሳቢያ ነዋሪዎች እና የከተማዋ አስተዳደር ወደ ቆቦ ከተማ መሰደዳቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8/2016 ዓ.ም፡- በቅርቡ በራያ አላማጣ አከባቢ ተከስቶ ከነበረው ግጭት ጋር በተያያዘ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች እና የከተማው አስተዳደር በአቅራቢያቸው ወደምትገኘው የአማራ ክልል ቆቦ ከተማ መሰደዳቸው ተገለጸ።

ከደቡብ ራያ አላማጣ እና አከባቢ ሸሽተው ትላንት ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.መ ወደ አማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ የገቡ ሰዎች ቁጥር ከ3 እስከ 5 ሺ ይደርሳል ያሉን የቆቦ ከተማ ነዋሪ፣ አቅም የሌላቸው በከተማዋ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ በሆነው ዕውቀት ጮራ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠልለው ማደራቸውን ነግረውናል።

ዛሬ ሚያዚያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ጠዋት የተወሰኑት ወደ መጡበት ሲመለሱ ማየታቸውን ገልጸዋል።

አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው የቆቦ ከተማ ነዋሪ እንደገለጹት አብዘሃኛዎቹ ከደቡብ ራያ አላማጣ አከባቢ ተሰደው በቆቦ ከተማ የሚገኙት ተፈናቃዮች አማርኛ ተናጋሪዎች እና ባለፉት ሁለት አመታት በአከባቢው የነበረውን አስተዳደር በስፋት ሲደግፉ የነበሩ በመሆናቸው ስጋት አድሮባቸው የመጡ ናቸው።

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ በበኩሏ ከአላማጣ የመጡ አምስት ሰዎችን ማስጠጋቷን እና እቤቷ ማደራቸውን ገልጻ ዛሬ ሚያዚያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም አላማጣ ለሚገኙት ቤተሰቦቻቸው ደውለው ምንም ነገር የለም መምጣት ይሻላችኋል ተብለው ለመመለስ እየተዘጋጁ ቢሆንም አብረዋቸው የተሰደዱ የአከባቢው አመራሮች ግን ነገሩ እስኪጣራ በሚል ቆዩ እንዳሏቸው ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቃለች።

በከተማዋ የሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ከነትጥቃቸው የመጡ የአከባቢው ሚኒሻ አባላት ትጥቃችሁን አስቀምጣችሁ ወደ ቤታችሁ መግባት ትችላላችሁ እናደራድራችሁ ሲሉ ቢገልጹላቸውም እነሱ ከነትጥቃቸው ገበተው አኛ ትጥቅ ፈትተን አንመለስም አናምናቸውም የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው በምክክሩ ላይ መሳተፋቸውን የገለጹ የቆቦ ከተማ የሀገር ሽማግሌ ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቀዋል።

የአላማጣ እና የኮረም ከተማ ነዋሪዎች የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከተሞቹን ተቆጣጥሮ በማስተዳደር ላይ ይገኛል ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ አረጋግጠዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ትላንት ከተማዋን ጥለው ሂደው የነበሩ አንዳንድ የከተማዋ አስተዳደር አባላት መመለስ ጀምረዋል ሲሉ ገልጸዋል።

በአከባቢው ነዋሪ የነበሩ እና የትግራይ ተወላጆች እየሆኑና ላለፉት አመታት ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ በመመለስ ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

የግጭቱ መንስኤ ዙሪያ ነዋሪዎች እና የአከባቢው ባለስልጣናት የተለያዩ መረጃዎችን በመስጠት ላይ ይገኛሉ፣ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞላ ደርበው እና የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ግጭቱ የተጀመረው የህወሓት ሀይሎች በመተናኮሳቸው ነው ብለዋል።

ተኩስ የከፈቱት በወረዳው አዲስ ብርሃን (በቀድሞ ስሙ ላዕላይ ድዩ) በተባለ ቀበሌ በኩል መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በትግራይ ክልል የደቡባዊ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ሀፍቱ ኪሮስ፤ ቅዳሜ እና እሁድ የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዲተገበር የሚጠይቁ የራያ አካባቢ ተፈናቃዮች “ረጅም ርቀት በእግራቸው በመጓዝ” ሰልፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል። ከመሆኒ እና ከማይጨው ከተሞች በመነሳት የተደረጉት ሰልፎች “የመከላከያ ሠራዊት ኬላ እስከሚገኝባቸው አካባቢዎች” የተደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

አቶ ሀፍቱ፤ “ድምጻችንን እያሰማን ባለንበት ወቅት ታጣቂዎች፤ ታኦ ከሚባል አካባቢ ተሰባስበው የእኛ ሚሊሻዎች ወዳሉበት አካባቢ [መጥተው] ለተኩስ የተጋበዙበት ሁኔታ ተፈጠረ” ሲሉ በሁለቱ አካላት መካከል ለተደረገው የተኩስ ልውውጥ ምክንያት የሆነውን ክስተት ጠቅሰዋል።

ይህንን ተከትሎ “ግጭቶች” መፈጠራቸውን የሚናገሩት የደቡባዊ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፤ “ከእኛ ሚሊሻዎች ጋር ግጭት ተፈጠረ፤ [ከእኛ በኩል የነበሩት] ሚሊሻ እና ፖሊስ ናቸው። ሌላ ምንም ሌላ ዓላማ የነበረው አይደለም” ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ግጭቱ በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ወይም በሕወሃት ወይንም በትግራይ እና በአማራ ክልሎች መካከል የተፈጠረ አይደለም ብለዋል።

በደቡብ ትግራይ እና በሌሎች የትግራይ ክልል ግዛቶች ባሁኑ ወቅት ለተፈጠረው ግጭት የፕሪቶሪያው ስምምነት ጠላቶች የፈጠሩት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ሁኔታውን አስመልክቶ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን ትላንት ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “ከትናንት ታሪካዊ ስህተቱ የማይማረው ህወሐት ለአራተኛ ዙር በህዝባችን ላይ ወረራ ፈፅሟል” ሲል ኮንኗል።

የፌዴራልና የአማራ ክልል መንግስታትም “በህዝብ ላይ የተቃጣውን የጥፋት ወረራ በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ” ሲል አሳስቧል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button