ዜናፖለቲካ

ዜና፡ አራተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር በአዲስ አበባ በማካሄድ ላይ ይገኛል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8/2016 .ም፡ በአዲስ አበባ በኢትዮጵያ ግብጽ እና ሱዳን መካከል አራተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ።

ኢትዮጵያን የወከለው ተደራዳሪ ቡድን መሪ የሆኑት አምባሳደር ስለሺ በቀለ በይፋዊ የኤክስ ማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ያጋሩት መረጃ እንደሚያመላክተው በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ያለው የሶስትዮሽ ድርድር በቀደሙት ግዜያት በነበሩ ድርድሮች የተካሄዱ ውይይቶችን ለማጎልበት ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።

የቴክኒክ ቡድኑ ያቀረባቸውን ነጥቦች ከቀደሙ ውይይቶች እና ከሚኒስትሮች ውይይት ጋር አጣምሮ የጋራ ውጤት ለማስገኘት ጥረት እንደሚደረግም አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የተፈረመውን የመርህ ስምምነት መሰረት በማድረግ ወደ ድርድር መግባቷን አምባሳደሩ በመረጃቸው አመላክተዋል። ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ ላይ ያላትን የጋራ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት አቋም አሁንም ታራምዳለች ብለዋል።

በግብጽ ካይሮ ተካሂዶ የነበረው ሶስተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር “ድርድሩ መጠነኛ መሻሻል እና መግባባት” የታየበት ነበር ሲሉ  በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደርና የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን መሪ አምባሰደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በወቅቱ መናገራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

የግድርድሩ ሂደት አሁንም እንደሚቀጥል እና አራተኛው ዙር የሶስትዮሽ ድርድር በታህሳስ ወር በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ማስታወቁም በዘገባው ተካቷል።

ጥቅምት 12 እና 13 ቀን 2016 ዓ.ም በግብጽ ካይሮ የተካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ለሶስተኛ ግዜ የተካሄደ ሲሆን የድርድሩ ዋነኛ ትኩረት በግድቡ ውሃ ሙሌትና አለቃቀቅ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ እንደነበር ሚኒስቴሩ በመግለጫው አመላክቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ በግብጽ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ጋር ከተወያዩ በኋላ የድርድሩን ሂደት በአራት ወራት ውስጥ ለመቋጨት መስማማታቸው መገለጹን ተከትሎ የመጀመሪያው እና ሶስተኛው ዙር ውይይት በካይሮ፣ ተካሂዷል:: ሁለተኛው እና በመካሄድ ላይ ያለው አራተኛው ዙርን ድርድር ያስተናገደችው አዲስ አበባ ናት።

በቀደሙት ውይይቶች ስኬት ያልመጣው በኢትዮጵያ ያልተቀየረ አቋም ምክንያት ነው ስትል ግብጽ በተደጋጋሚ ክስ ስታቀርብ መሰንበቷ ይታወቃል።

በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚካሄዱ ድርድሮች በቅርቡ በስምምነት እንደሚቋጩ ያላቸውን ተስፋ የተባበሩት አረብ ኤሚሬት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሸክ ሻህቡት ናህያን አል ናህያን ባሳለፍነው አመት ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል። ስምምነቱ የሶስቱን ሀገራት ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ይሆናል የሚል እምነታቸውንም አጋርተዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button