ዜናፖለቲካ

ዜና፡ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ውጥረት በማርገብ እንዲወያዩ አሜሪካ ጥሪ አቀረበች

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25/2016 .ም፡ የአሜረካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ መካከል የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙን ተከትሎ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በመካከላቸው የተፈጠረውን ውጥረት በማርገብ እንዲወያዩ ጥሪ አቅርቧል።

በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ መካከል የተፈረመውን ስምምነት ተከትሎ  የመንግስታቸው አቋም ምን እንደሆነ የተጠየቁት የመስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር ከቀጠናው የሚወጡ ሪፖርቶች የሜሪካን መንግስትን እንደሚያሳስቡት በመግለጽ እንደሌሎቹ አጋሮቻችን ሁሉ ያደረብንን ስጋት መግለጽ እንፈልጋለን ብለዋል።

በተጨማሪም ቃል አቀባዩ የአሜሪካ መንግስት ሶማሊያ በ1960 ያገኘችውን የግዛት አንድነት እና ወሰን እንደመያከብር አስታውቋል።

ቃል አቀባዩ መንግስታቸው የተፈረመው የመግባቢያ ሰነዱን እንደሚቀበለውም ይሆን እንደማይቀበለው በቀጥታ ከመመለስ ተቆጥበዋል። ባለድርሻ አካላት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ልዩነቶቻቸውን እንዲፈቱ ማሳሰብ እንወዳለብ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

በሌላ መልኩ የአዉሮፓ ህብረት ባወጣው መግለጫ የሶማሊያ ሉዓላዊነት ሊከበር ይገባል ሲል በማሳሰብ የሶማሊያ የድንበር ወሰን፣ አንድነቷ እና የሀገሪቱ ክብር ሊጠበቅ ይገባል ማለቱ ይታወሳል።

ኢጋድ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ሁኔታ በጥንቃቄ እየተከታተለው እንደሚገኝ በመግለጽ በቀጠናው ሰላም ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ እንደሚገነዘብ ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።  ኢጋድ በመግለጫው  ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስለተፈራረሙት መግባቢያ ሰነዱ ያለው ነገር የለም። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button