ዜናማህበራዊ ጉዳይ

ዜና፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአርሲ በተከታዮቿ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አወገዘች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 25/2016 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአርሲ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች በኦርቶዶክሳውያን ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት በማውገዝ የጸጥታ ተቋማትም ጥቃቱን እንዲከላከሉ ስትል ጠየቀች።

ቤተክርስቲያኗ በጠቅላይ ጽህፈት ቤቷ በኩል ባወጣችው መግለጫ በአርሲ ዞን በሹርካ ወረዳ ሶሌ ሚካኤል፣ በዲገሎ ማርያም፣ በሮቤ እንደቶ ደብረ ምጥማቅ ማርያም አብያተክርስቲያናት ላይ በተለያዩ ጊዜያት 36 ኦርቶዶክሳዊያን በደረሰባቸው ጥቃት ሕይወታቸውን ማጣታቸውን አስታውቃለች።

በዚሁ ጥቃት በሶሌ ዲገሉ እና ጢጆ ለቡ በተባሉ ቀበሌዎች 28 ኦርቶዶክሳዊያን ከየቤታቸው ተለቅመው ተገድለዋል ያለው መግለጫው ከእነዚህ ውስጥም 7ቱ ሴቶችና 21ዱ ወንዶች መሆናቸውንም ጠቁሟል።

በዚህ ጥቃትም እድሜያቸው ከሰባ ዓመት አዛውንት እስከ ሃያ ስምንት ቀን ጨቅላ ሕጻናት እንደሚገኙበት ቤተክርስቲያኗ በመግለጫዋ አስታውቃለች።

ህዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም ደግሞ በዲገሉ ማርያም ቤተክርስቲያን 5 ኦርቶዶክሳዊያን ከመገደላቸው በተጨማሪ የሦስት ኦርቶዶክሳውያን ቤት መቃጠሉን ያመላከተው መግለጫው ከዚህ ቀደም በሮቤ አንዲቶ ደብረ ምጥማቅ ማርያም ቤተክርስቲያን በዓለ ማርያምን አክብረው ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ የነበሩ ሦስት ኦርቶዶክሳዊያን ጨለማን ተገን ባደረጉ ነፍሰ ገዳዮች መገደላቸውን አውስቷል።

የመንግሥት የጸጥታ አካላት በዚህ ዐይነት የጥቃት ተግባር ላይ ተሰማርተው የሚገኙ አንዳንድ አካላት ላይ በመንግሥት በኩል የማያዳግም ርምጃ እንደተወሰደባቸው ሀገረ ስብከቱ በላከው ሪፖርት ማረጋገጡን የቤተክርስቲያኗ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ድርጊቱን በማውገዝ ችግሩ ከመሠረቱ እንዲፈታ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር መፍትሔ መፈለግ ሲገባው በዝምታ በማለፉ ቤተክርስቲያን ከፍተኛ ቅሬታ ተሰምቷታል ሲል ተችቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ጉዳዩን ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር  በመሆን እንደሚከታተለው ጠቁሟል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button