ጥልቅ ትንታኔፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ጥልቅ ትንታኔ፡ በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው ክፍፍል የትግራይን ሰላምና መልሶ የማገገም ሂደት አደጋ ላይ እየጣለ ይገኛል

በሞላ ምትኩ @MollaAyenew

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10/ 2017 ዓ/ም፦ በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አብይ ሚና የነበረው ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፤ በአሁኑ ወቅት የትግራይ ክልልን መረጋጋትን አደጋ ላይ ከሚጥል እና የመልሶ ግንባታ ጥረትን ከሚያደናቅፍ ከባድ ውስጣዊ ክፍፍል ገብቶ እየታገለ ይገኛል።

እነዚህ ውጥረቶች፤ ለሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት ሳቢያ በተከሰተው መፈናቀል እና ሰብአዊ ቀውስ ተጎጂ የሆነው የክልሉ ህዝብ ላይ ተጨማሪ ስጋቶች አስከትለዋል።

ምንም እንኳ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ህዳር 2022 በአፍሪካ ጥላ ስር የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ቢከናወንም፤ የፓርቲው ውስጣዊ አለመግባባቶች እና ህጋዊ ሰውነቱን በማስመለስ ረገድ ያልተፈቱ ጉዳዮች መኖራቸው ሁኔታውን የበለጠ አባብሰዋል። 

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በህወሓት ውስጥ ያለው መከፋፈል እየተባባሰ  በመምጣቱ፤ በፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል  እና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ በሚመሩ ሁለት ቡድኖች መካከል ከፍተኛ ልዩነት ተፈጥሯል። 

አንደኛው ቡድን የሌላውን ቅቡልነት ለማሳጣት በሚያደርጉት ጥረት  ውስጣዊ ግጭቱ  እየተባባሰ መጥቷል። በዚህም ምክንያት ቀድሞውኑ ከሰብዓዊ ቀውስ ጋር እየታገለ ያለው ክልሉ፤ በመሰረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት ውስንነት እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀለ ሳቢያ ለተጨማሪ አለመረጋጋት ተዳርጓል።  የፓርቲው ክፍፍል በህዝቡ ዘንድ  የጥርጣሬ እና የፍርሃት ድባብ በመፍጠር የተጠቀሱትን  ተግዳሮቶች ለመፍታት  የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ አደናቅፎታል። 

አንዳንድ ምሁራን በህወሓት ውስጥ የተፈጠረውን መከፋፈል በፓርቲው የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የተለመደ ባህሪ አድርገው ቢመለከቱትም የትግራይ ህዝብ ግን ይህ ውዝግብ በዝህ ወቅት መከሰቱ ሊያስከትለው ስለሚችለው ውጤት በእጅጉ ያሳስበዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የትግራይ ክልል መዲና መቐለ ነዋሪ በክልሉ የተከሰቱትን አሰቃቂ ክስተቶች ተከትሎ የአመራሩ መከፋፈል እንዳሳዘናቸው ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

“ይሁን እንጂ የፀጥታ ሀይሎች ገለልተኝነታቸውን እንደሚጠብቁ እና አመራሮቹ ልዩነቶቻቸውን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንዲችሉ አሳስበው ይህንን ማድረግ ካልቻሉ ግን ህዝቡ የፈለገውን ወገን የመደገፍ ነፃነት እንዲኖረው እንደሚፈቅዱ እርግጠኞች ነን” ብለዋል።

ሌላኛው ስማቸው ኢንዲጠቀስ ያልፈለጉ የመቀለ ከተማ ነዋሪ፤ በትግራይ ያሉ የፖለቲካ አመራሮች “ህልውናቸው የማስቀጠል ጉዳይ ልዩነታቸውን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ላይ የተመርኮዘ የመሆኑን  እውነታ መረዳት አልቻሉም” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

“ህወሓት ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ ይገኛል” ያሉት ነዋሪው፤ “መግባባት ላይ የማይደርስ ከሆነ ግን የትግራይን ህዝብ ወደ አስከፊ ሁኔታ ማስገባቱ  የማይቀር ነው” ይላሉ።

የውስጣዊ አለመግባባት መባባስ 

ምሁራን እና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፤ የህወሓት አመራሮች ልዩነቶቻቸውን መፍታት ባለመቻላቸው ከፍተኛ ስጋት እንዳደረባቸው በመግለጽ እየተከሰቱ ያሉት ግጭቶቹ ቀድሞውኑ በክልሉ የተከሰተቱትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውሶችን የበለጠ ሊያባብሱ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

እነዚህን ስጋቶች ያስተጋቡት የመቀለ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ገብረመድህን ያለው፤ አንዳንድ የደቡብ ትግራይ ነዋሪዎች የዶክተር ደብረፂዮንን ቡድንን ሲደግፉ፣ በአድዋ እና በሽሬ ካሉ ነዋሪዎች መካከል ደግሞ የአቶ ጌታቸውን ቡድን ደጋፊ መኖራቸው  ጠቁመዋል። 

እንደ ገብረመድህን ገለጻ፤ ይህ የሚያመላክተው አመራሩ ህዝቡን በከባቢያዊነት ለመከፋፈል የሚያደርገውን ማንኛውንም ሙከራ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እንደሌለው ነው። 

“የህወሓት የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወሰነው በመሪዎቹ ልዩነታቸውን መፍታት አቅም እና ለተሻለ ነገር በመተባበር ላይ በሚኖራቸው ችሎታ  ነው” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

በቅርቡ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ የቀድሞ የዞን አስተዳደሮችን በመሻር አዳዲስ ኃላፊዎችን መሾማቸውን ተከትሎም በሁለቱ ህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ተባብሶ ቀጥሏል።

በምላሹም የህወሓት ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር በጻፉት ደብዳቤ፤ የተሰጠውን ሹመቶች ውድቅ አድርገዋል። 

ይህን ተከትሎም፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ከፕሬዝዳንት እውቅና/ፍቃድ/ ውጭ ስብሰባ እንዳይካሄድ ክልከላ ጥሏል።

የመቀለ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪው ገብረመድህን፤ “ይህ ውስጣዊ አለመግባባት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያመለክት ነው፤  የክልሉ መጻዒ ዕጣ ፈንታ ላይ ስጋት ይጥላል” ይላሉ። “ትግራይ አሁን በተስፋ እና በተስፋ መቁረጥ መካከል በሆነ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፤ እናም በከፍተኛ አመራሮች መካከል ያለው የስልጣን ሽኩቻ አለመረጋጋትን ከማባባስ ባለፈ የክልሉን መልሶ የማጠናከር ጥረቶችን ያደናቅፋል” ሲሉ ገልጸዋል። 

ተመራማሪው፤ ከሰብዓዊና የጸጥታ ችግሮች በተጨማሪ የውስጥ ግጭት ዋነኛ የስጋት ምንጭ እየሆነ መምጣቱን አስምረውበታል።

በፖለቲካ አመራሮች መካከል ያለው የስልጣን ሽኩቻ እየተባባሰ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች የተናጠል ስብሰባ በማድረግ አንዱ ሌላኛውን የፓርቲውን ህግና ደንብ ጥሷል እያሉ ይካሰሳሉ ብለዋል።

የህወሓት 14ኛ ጉባዔ፡ ፎቶ ህወሀት ፌስቡክ ገጽ

በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ቡድን፤ በህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፂዮን በ14ኛው የህወሓት ጉባኤ የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ጌታቸውን በቀድሞ የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አማኑኤል አሰፋ በመተካት ያሳለፉት ውሳኔ ተቀባይነት የለውም ሲል ገልጿል። 

የድርጅቱ ጉባኤ የተካሄደው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፍቃድ ውጭ የተካሄደ ሲሆን፤ ቦርዱ በጉባኤው ላይ ለሚወሰኑ ውሳኔዎች በሙሉ ዕውቅና የማይሰጥ መሆኑን አስታውቋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህውሓት) ከጦርነቱ በፊት የነበረው ህጋዊ ሰውነት በልዩ ሁኔታ እንደ አዲስ እንዲሰጠው ሳይሆን የነበረው እንዲመለስለት ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርጎታል። ይህንንም በደብረፂዮን የሚመራው ቡድን ተቃውሞታል። 

ያልተፈታው የህወሃት ምዝገባ ጉዳይ ዋና አከራካሪ ነጥብ ሆኖ ቀጥሏል ይህም የሁለቱን ቡድን ልዩነት የበለጠ እያሰፋውም ይገኛል። መስከረም 6 ቀን ህወሓት ባወጣው መግለጫ፣ ምክትል ሊቀመንበሩን ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 16 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱን ማባረሩንና ከድርጅታዊ ሃላፊነታቸውና በጊዜያዊ አስተዳደሩ ካላቸው ውክልና በሙሉ ማንሳቱን አስታውቋል። ማዕከላዊ ኮሚቴው አሰናብቻቸዋለሁ ያላቸውን አባላቱን በሙስና ወንጀል ጭምር እንደሚጠይቃቸው ገልጧል። 

የትግራይ መጻዒ እጣ ፈንታ

ገብረመድህን በህወሓት ውስጥ እየተካሄደ ያለው የውስጥ ግጭት በትግራይ ህዝብ መካከል ከፍተኛ ውጥረት እና እርግጠኛ ያለመሆን ስሜትን እያሰፋ በመሆኑ የክልሉን አስከፊ ሰብዓዊ ቀውስ የበለጠ እያባባሰው መሆኑን ገልጸዋል።

በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ጦርነቱ ቢቋጭም፤ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተፈናቃዮች ለከፋ የምግብ እጥረት፣ ለጤና ጥበቃ አገልግሎት ተደራሽነት ውስንነት የተጋለጡ ሲሆን እገታ፣ ግድያ እና ጾታዊ ጥቃትን ጨምሮ በርካታ ጥቃቶች እየተከሰቱ  ይገኛሉ።

አቶ ጌታቸው ከአዲግራት ከተማ ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ተፈናቃዮችን ለመመለስ እና ሌሎች ስራዎችን ለማከናወን በርካታ ተግዳሮቶች መኖራቸውን አረጋግጠዋል። 

መምህር እና ተመራማሪው ገብረምድህን በውስጣዊ የስልጣን ሽኩቻ ስር የሰደደው የድርጅቱ አመራሮች ክፍፍል በክልሉ ያለውን የሰብዓዊ ቀውስ ሊያባብሰው እንደሚችል ገልጸዋል።

ይህ የውስጥ ክፍፍል በትግራይ ክልል ላይ ካለው ተጽእኖ ባሻገር ፓርቲው እንደ ፌዴራል መንግስት ካሉ የውጭ አካላት ጋር በብቃት ለመደራደር ያለውን አቅም በእጅጉ የሚጎዳ መሆኑንም ተመራማሪው አስረድተዋል።

የገብረመድህንን ስጋት የሚጋሩት የውድብ ናፅነት ትግራይ ፓርቲ ነባር አባል የሆኑት መሃሪ ግርማይ (ዶ/ር) ሁለቱ ወገኖች በፌዴራል መንግሥት ላይ ያላቸው የተለያየ አመለካከት የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን ከማስቆም ባለፈ ህወሓት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለውን አቅም ያዳክማል ብለዋል።

አክለውም ክፍፍሉ ወደ አደገኛ ሁኔታ ሊሸጋገር እንደሚችል አስጠንቅቀው፤ አንደኛው ወይም ሁለቱም ወገኖች ከውጭ ኃይሎች ለምሳሌ ከፌዴራል መንግሥት ወይም ከኤርትራ ድጋፍ ሊሹ ይችላሉ ሲሉ ገልጸዋል። 

“ይህም ክልሉን ዳግም ወደ ግጭት ሊያስገባው ይችላል” ሲሉ ዶ/ር መሃሪ አስጠንቅቀዋል። 

ባሳለፍነው ሳምንት ደብረፂዮን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የህወሃት አመራሮች ከኤርትራ ጋር ንግግር እያደረጉ ነበር ሲሉ ገልጸዋል።

የፓርቲው ሊቀመንበር፤ የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴዎች ባደረጉት ውሳኔ መሰረት በአቶ ጌታቸው ረዳ የተመራ የልዑካን ቡድን ከኤርትራ ጋር ድርድር ጀምሮ እንደነበር  አስረድተዋል።

አቶ ጌታቸው ከኤርትራ ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሪፖርት ካደረጉ በኋላ፣ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ኤርትራውያን በእናንተ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ አላቸው፤ ይህን ጉዳይ መፍታት አለባችሁ ብለዋል” ሲሉም ገልጸዋል።

ዶክተር መሃሪ  “ሁለቱም ወገኖች ከፌዴራል መንግስት ወይም ከኤርትራ መንግስት ድጋፍ ለማግኘት የውጭ ደጋፊዎች የህወሓትን ውስጣዊ ግጭት በማባባስ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል” ብለዋል።

አክለውም “እነዚህ የውጭ አካላት ውጥረትን በማቀጣጠልና የዕርቅ ጥረቶችን በማዳከም፤ ህወሓትን ተጠቅመው ክልሉን ወደ ጦርነት አውድማ ሊመልሱት ይችላሉ” ብለዋል።

“በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው ስር የሰደደ አለመተማመን ልዩነታቸውን በዘላቂነት ለመፍታት ፈታኝ አድርጎታል” ያሉት  መሃሪ “ሁለቱም ወገኖች በመወነጃጀል ቁልፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለመደራደር የሚኖራቸው አቅም ይዳከማል” ብለዋል።

ዶክተር  መሃሪ  “ሁለቱም ቡድኖች ችግሮቻቸውን ባለመፍታተቸው የሽግግር መንግስቱ  ክልሉን በአግባቡ እንዳያስተዳድር እንቅፋት ሆነዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

የመፍትሄ መንገድ

በትግራይ እየደረሰ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ በህወሓት ውስጥ እየተፈጠረ ያለው የአመራር ክፍፍል ምክንያት የበለጠ ፈታኝ እየሆነ በመምጣቱ፤ ለዘላቂ መፍትሄ የተጎጂውን ህዝብ ፍላጎት የሚፈታ፣ አሳታፊ ዲሞክራሲን የሚያጎለብት፣ እርቅን ማፋጠንና ሰብአዊ መብቶች መከበርን የሚያረጋግጥ አጠቃላይ አካሄድ እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።

በቅርቡ በትግራይ ክልል ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሀመር የህወሃት መሪዎችን በተናጠል በማግኘት በፓርቲው ውስጥ የተከሰተውን መከፋፈል በውይይት እንዲፈቱ አሳስበዋል። 

ዶ/ር መሃሪ በበኩላቸው፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ ሲቪክ ማኅበራት ድርጅቶችን እና አጠቃላይ ህዝቡን ጨምሮ በርካታ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ የመንግስት መዋቅር መመስረት አለበት ይላሉ

“ህወሓት የህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ ውሳኔዎች መተላለፋቸውን ለማረጋገጥ የመንግስትንና እና የፓርቲን ተግባር መለየት አለበት” ሲሉም ተገልጸዋል። “በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት የሚያሳትፍ አካሄድ መወሰድ አለበት” ነው ያሉት።

አክለውም የህወሃት መሪዎች ልዩነቶቻቸውን እንዲፈቱ እና ለትግራይ ህዝብ ደህንነት ቅድሚያ እንዲሰጡም አሳስበዋል።

“የግጭቱን ዋና መንስኤዎች ለመቅረፍ እና የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ፤ የክልል ምክር ቤት በአሳታፊ ሂደት ማቋቋም ወሳኝ ነው” ብለዋል።

መሃሪ እና ገብረመድህን የጸጥታ ሀይሎች ገለልተኝነታቸውን እንዲጠብቁ፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የአስታራቂነት ሚናን እንዲወጡ እና የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አለም አቀፍ ክትትል እንዲደረግበት ጥሪ አቅርበዋል።

ሰላምን በማስፈን ረገድ የዳያስፖራው እና የመገናኛ ብዙሃን ሚና ወሳኝ መሆኑንም አስምረውበታል።

በተጨማሪም የህወሓት የውስጥ ክፍፍል ጉዳይ መፈታት፤ በክልሉ ያሉትን ፈተናዎችን ለመቋቋም እና ለትግራይ ተስፋ ሰጪ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመቅረጽ እጅግ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button