ዜናፖለቲካ

ዜና: “ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሰላምና መረጋጋት በተገናኘ የሚቀርቡባትን ክሶችና ወቀሳዎች በፍጹም አትቀበልም” - አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18/2017 ዓ.ም፡- ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሰላምና መረጋጋት በተገናኘ የሚቀርቡባትን ክሶችና ወቀሳዎች በፍጹም አትቀበልም ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ አስታወቁ፤ ሽብርተኝነትን ከመዋጋት የሚያግዳት ምንም ነገር እንደሌለም ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ይህን የገለጹት በኒውዮርክ እየተካሄደ በሚገኘው 79ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኛነትን በመዋጋት ሰላምና ደህንነት እንዲረጋገጥ እየሰራች እንደምትገኝ የገለጹት አምባሳደር ታየ በሶማሊያ የሽብርተኛ ቡድን የሆነውን አልሻባብን አቅም በከፍተኛ ሁኔታ በማዳከም ረገድ ከሌሎች አገራት ሰላም አስከባሪ ሃይሎች ጋር ውጤታማ ተግባር ማከናወኗን አመልክተዋል።

በሶማሊያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት የተገኙ ድሎችን ስጋት ላይ የሚጥሉ ጉዳዮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋሉ መምጣታቸውንም ተናግረዋል።

ዓለም አቀፋ ማህበረሰብ በሶማሊያ የተገኙ ድሎችን ወደ ኋላ በመመለስ የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት ስጋት ላይ የሚጥሉ  ድርጊቶችን ሊያስቆም እንደሚገባ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ አሳስበዋል።

አምባሳደር ታዬ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም የከፈለችውን መስዋዕትነትና ዋጋ እውቅና ልትሰጥና ልታከብር እንደሚገባም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ እንዲሁም ለውጤታማ የባለብዙ ወገን የትብብር መድረክ በቁርጠኝነት ትሰራለች ብለዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት ከቀጣናው አገራት ጋር አብሮ መልማትና ማደግን መሰረት ያደረገ ነው ሲሉ  አምባሳደር ታዬ አስታውቀዋል። ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት እና የማሪታይም ንግድን የምትጠቀመው ኢትዮጵያ በውቅያኖሶቹ ያለውን የማሪታይም ደህንነት በቅርብ እንደምትከታተል ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የማሪታይም ደህንነት ጥበቃ ስራዎች ሁሉን አሳታፊ እንዲሆኑ ትፈልጋለች ያሉት አምባሳደር ታዬ የባህር በር የማሰስና የመጠቀም ፍላጎቷ ሊከበር እንደሚገባም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው ስምምነት ከቀጣናው አገራት ጋር በጋራ መልማትና መበልፀግን መሰረት ባደረገ መልኩ መሆኑን አስታውቀዋል።

አምባሳደር ታዬ በንግግራቸው አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቋሚ ውክልና ማግኘት እንደሚገባት ገልጸዋል።

የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ወደ ታሪካዊው የትግበራ ምዕራፍ ሊሸጋገር መቃረቡን ገልጸው ይህም በተፋሰሱ አገራት ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲኖር ያደርጋል ነው ያሉት።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት መጀመሩንና ይህም የኢትዮጵያንና የጎረቤት አገራትን የኤሌትሪክ ኃይል ፍላጎት በመመለስ ቀጣናዊ ትብብርን ለማጎልበት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ መግለጻቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያሳያል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button