ዜናፖለቲካ

ዜና: ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ወደ ፑንትላንድ "ሉዓላዊነቴን በመጣስ ያልተፈቀደ የጦር መሳሪያ ዝውውር" ተደርጓል ስትል ከሰሰች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11/2017 ዓ.ም፡- የሶማሊያ መንግስት በኢትዮጵያ በኩል ወደ ሶማሊያዋ የፑንትላንድ ግዛት “ሉዓላዊነቴን በመጣስ ያልተፈቀደ የጦር መሳሪያ እና ተተኳሽ ጥይቶች ዝውውር” አካሂዷል ሲል ክስ አቀረበ።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር መስከረም 10 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጸው ሁለት የጭነት መኪናዎች ከኢትዮጵያ ወደ ፑንትላንድ “ያለምንም ዲፕሎማሲያዊ ተሳትፎ ወይም ፍቃድ” የጦር መሳሪያ ሲጓጉዙ እንደነበረ የሚያሳዩ “የተረጋገጡ ሰነዶች” መኖራቸውን ገልጿል።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ክስተቱን “በሶማሊያ ሉዓላዊነት ላይ የተፈጸመ ከፍተኛ ጥሰት” በማለት ጠቅሶ ይህም “ለሀገራዊ እና ክልላዊ ደህንነት አሳሳቢ አንድምታ” ያለው ነው ሲል ገልጿል።

የሶማሊያ መንግስት ይህ የተናጥል ክስተት እንዳልሆነ ጠቁሞ ከዚህ ቀደም “መሳሪያዎች በተመሳሳይ መልኩ ወደ ጋልሙዱግ ክልል መጫናቸውን እና ሌሎች የመሳሪያ ክምችቶች በድብቅ በአውሮፕላኖች ወደ ባይዶዋ መግባታቸውን አንስቷል።

የሶማሊያ መንግሥት እነዚህን ክስተቶች፣ “የሶማሊያ ሉዓላዊነትን ቀጣይነት ባለው መልኩ ትኩረት የነፈጉ” ሲል ገልጿል።

እነዚህ ውንጀላዎች የቀረቡት በኢትዮጵያ እና በራስ ገዟ ሶማሌላንድ መካከል በጥር ወር 2016ዓ.ም. የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት በሻከረበት በዚህ ወቅት ነው።

ቱርክ በሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ ጎረቤት ሃገራት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ያለሙ ሁለት ዙር ስብሰባዎችን ብታስተናግድም እስካሁን ምንም ውጤት አልተገኘም።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የአሁኑ ክስ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው በሺይላማው የአከባቢው ሚሊሻዎች የጦር መሳሪያዎችን የጫኑ መኪኖችን መያዛቸውን ተከትሎ በሶማሊያ በኩል የተነሱትን ስጋቶች የሚያስተጋባ ነው።

ኢትዮጵያ በበኩሏ በሶማሊያ ባለስልጣናት በኩል እየተሰጡ ናቸው ያለቻቸውን “ያልተፈለጉ እና ኃላፊነት የጎደላቸው መግለጫዎች”ን “አሳዛኝ” ስትል ለነዚሁ አቤቱታዎች ምላሽ ሰጥታለች።

የሱማሊያ መንግሥት ባወጣው መግለጫ እነዚህ ድርጊቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ የጠየቀ ሲሆን ቀጠናዊና ዓለማቀፍ አጋሮች ጉዳዩን አጽንኦት እንዲሰጡት ጠይቋል።

በተጨማሪም የሶማሊያ መንግስት ችግሩን በ”ዲፕሎማሲያዊ ውይይት” እና “በትብብር ማዕቀፎች” ለመፍታት ያለውን ምርጫ አፅንዖት እንደሚሰጥ ገልጿል።

እነዚህ ክስተቶች የተፈጠሩት የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት እ.ኤ.አ. ከ1992 ጀምሮ በሶማሊያ ላይ ጥሎት የነበረውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ካነሳ ከአንድ አመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ነው። የሶማሊያ መንግስት ሀገሪቱን ከታጠቁ ሚሊሻዎች እና ከአልሸባብ ታጣቂዎች ለመቆጣጠር እየሰራ ይገኛል ተብሏል።

በወቅቱ በሶማሊያ የፑንትላንድ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር የእገዳውን መነሳት “ሀገሪቱ የተከፋፈለች እና የተበታተነች” በመሆኗ “ትልቅ ስህተት” ነው ማለቱ ይታወሳል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button