ዜናፖለቲካ

ዜና: “የጊዜያዊ አስተዳደሩ የትግራይ ሰራዊትን በስሩ በማድረግ ማዘዝ አይችልም” ሲል በደብረጺዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ህወሓት አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15/2017 ዓ.ም፡- የጊዜያዊ አስተዳደሩ “የትግራይ ሰራዊትን በስሩ በማድረግ ማዘዝ አይችልም” ሲል በደብረጺዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ህወሓት ገለጸ፤ በጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ያሉ መሰረታዊ ችግሮችን ለመፍታት ወደ ተግባር እገባለሁ ሲልም አስታውቋል።

በደብረጺዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ትላንት መስከረም 14 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የትግራይ ሰራዊትን በስሩ በማድረግ ማዘዝ አይችልም ሲል ገለጸ።

“በጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ያሉ መሰረታዊ ችግሮችን ለመፍታት ወደ ተግባር እገባለሁ” ሲልም አስታውቋል።

በደብረጺዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው የህወሓት ቡድን ትላንት የሰጠው መግለጫ በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ “የክልሉ የጸጥታ አካላት በስሬ ሁነው እየተመሩ ይሰራሉ” ሲል ላወጣው መግለጫ የሰጠው ምላሽ ነው።

በደብረጺዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ህወሓት በትላንት መስከረም 14 መግለጫው “ጊዜያዊ አስተዳደሩ ስሙ እንደሚያመለክተው አስተዳደራዊ ስራዎችን እያከናወነ በአጭር ግዜ እንደመሸጋገሪያ የሚያገለግል እንጂ የትግራይ ሰራዊትን በስሩ አድርጎ በዕዝ ሰንሰለት ለመምራት የተሰጠው ተልእኮ፣ መዋቅርም ሆነ አደረጃጀት የለውም” ሲል ገልጿል።

ለዚህም ባስቀመጣቸው ምክንያቶች መካከል ጊዜያዊ አስተዳደሩ የተቋቋመው “የፕሪቶሪያ ስምምነትን ለማስፈፀም እና አስተዳደራዊ አገልግሎቶችን ለመስጠት ልንጂ የማይገባውን ስልጣን ለራሱ እየጨመረ፣ ራሱን ወደ መደበኛ ሀገራዊ  መንግሥትነት ቀይሮ ሠራዊቱን መምራት አይችልም” የሚለው ይገኝበታል።

በተጨማሪም አሁን ባለው አደረጃጀት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግስቱ መሆኑን ያመላከተው መግለጫው የትግራይ ሰራዊት በጊዜያዊ አስተዳደሩ ስር እንዲሆን ማድረግ ማለት “በስልጣን ሰንሰለታዊ ግንኙነት በፌደራል መንግስቱ ስር በማስገባት ማንኛውንም ትዕዛዝ እንዲቀበል የሚያደርገው አደገኛ አደረጃጀት የሚያስይዘው ነው” ሲል አስታውቋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የትግራይ ሰራዊት በጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ “የራሱ ተሳትፎና ድርሻ ያለው አንድ አካል እንጂ በተለያዩ አካላት ተወጣጥቶ በተቋቋመው አስተዳደር ስር ተካቶ አስፈፃሚ የሚሆን አካል አይደለም” ሲል አትቷል።

የትግራይ ሰራዊት “እልባት ላልተገኘለት የትግራይ ህዝብ ትግል፣ በሰላማዊና በፖለቲካዊ መንገድ እንዲያበቃ፣ በዲዲር (DDR) ሂደት ወደ ቀድሞ ኑሮው ለመመለስ የሚጠባበቅ ሃይል እንጂ እንደ ፖሊስ ወይም ሚሊሻ በጊዜያዊ አስተዳደር ስር ሁኖ ተልዕኮ በመቀበል የሚፈጽም የመንግስት አካል ወይም ሰራተኛ አይደለም” ብሏል። “በአጭሩ የተግራይ ሰራዊትን ለመበተን የተጎነጎነ ሴራ ነው” ሲልም ገልጿል።

በዚህ የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ደረጃ የትግራይ ሰራዊት የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ሃይሎች አጋር እንጂ የግዚአዊ አስተዳደሩ አስፈፃሚነት ተልዕኮ ያለው አካል አይደለም ያለው መግለጫው ስለዚህ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋናውን ተዋጊ ሃይል ሰብስቦ ማዘዝ አይችልም ሲል አስጠንቅቋል።

ህወሓት በጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ያሉ መሰረታዊ ችግሮችን ለመፍታት ወደ ተግባር ይገባል ሲልም አስታውቋል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት አፈጻጸምን ላይ “ከማተኮር ይልቅ ወደ ጎን በመተው ከተሰጠው ተልዕኮ እና ሀላፊነት ውጭ ተጠልፎ የግለሰቦችን ስልጣን ለማደላደል በሚያስችል ተንኮል ላይ ተጠምዷል” ሲል ገልጿል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ እራሱን እንደተመረጠ “መደበኛ መንግስት አስቦ ስልጣኑን ለማደላደል እንዲያመቸው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ ስም መግለጫ አውጥቷል” ሲል ተችቷል።

የደብረጺዮኑ ህወሓት ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ መግለጫም በሰጠው ምላሽ “በአሁኑ ወቅት ክልሉ ያጋጠመው ችግር በህወሓት ውስጥ ያለ ችግር ብቻ አድርጎ ለማቅረብ እየተደረገ ያለው ጥረት ተቀባይነት የለውም” ሲል አስታውቆ “ኢህአዴግን ከውስጥ እንዳፈረሱት ሁሉ አነዚህ ሀይሎችም በህወሓት ውስጥ ሁነው ፓርቲውን ለማፍረስ ቢጥሩም ስላልተሳካላቸው አሁን ደግሞ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ተሸፍነው እየተንቀሳቀሱ ነው” ሲል ኮንኗል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ “ግልጽ እና ውስን ተልዕኮ ተሰጥቶት እንደ የሽግግር ሂደት ሆኖ የሚያገለግል እንጂ ሙሉ የመንግስት ስልጣንና ሃላፊነት የለውም” ያለው መግለጫው የትግራይ ህዝብ የራሱ በራሱ የማስተዳደር መብቱን ተጠቅሞ መንግስት በምርጫ እስኪመሰርት የተሰጠው ተልዕኮ” አለው ሲል በዝርዝር አስቀምጧል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ተልዕኮም “ሰላምና ፀጥታን ማስጠበቅ፣ ማገገምና መልሶ ማቋቋም ስራ መስራት፣ የፕሪቶሪያ ስምምነትን በአግባቡ መተግበር፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እና በአጭር ጊዜ ገደብ ውስጥ በክልሉ በዲሞክራሲያ መንገድ በህዝብ የተመረጠ መንግስ እንዲመሰረት ሁኔታዎችን ማመቻቸት እና ምህዳር መፍጠር ነው” ሲል አስታውቋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም አካሄድኩት ባለው መደበኛ ስብሰባ በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ በመምከር ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ይፋ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል፤ ከውሳኔዎቹ መካከልም በክልሉ የሚገኙ “የጸጥታ አካላት እንደ አንድ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አካል” መሆናቸውን የጠቆመበት ይገኝበታል።

“አግባብነት ባለው ጥናት እና ምክክር እየተደረገበት በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት እና በካቢኔው እየተመሩ በህግ እና በስርአት ተልዕኮ እየተሰጣቸው ይፈጽማሉ” ሲል ማስታወቁም በዘገባው ተካቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button