ዜናማህበራዊ ጉዳይ

ዜና፡ የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበት እና የልማት ተነሺዎች የሚቋቋሙበት ረቂቅ አዋጅ ጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18/ 2016 ዓ/ም፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ሰኔ 18 ቀን ባካሄደው 34ኛ መደበኛ ስብሰባው፤  የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበትና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣ አዋጅን መርምሮ አጽድቋል፡፡

አዋጁ የመሬት ይዞታ እንዲለቁ ለተደረጉ ባለይዞታዎች ተገቢውንና ተመጣጣኝ ካሳና የተነሺ ድጋፍ ለመክፈል ግምት ውስጥ መግባት የሚገባቸውን መሰረታዊ ጉዳዮች ለይቶ ለመወሰን እንደሚያስችል የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገልጿል፡፡

እንዲሁም ካሳን ለመተመን፣ ለመክፈልና ተነሺዎችን መልሶ ለማቋቋም ስልጣንና ሀላፊነት ያላቸውን አካላት በግልጽ ለይቶ ለመወሰን የሚያስችል ስርዓት የዘረጋም ነው ተብሏል፡፡ አዋጁ ለልማት ተነሺዎች የሚከፈለውን ካሳ በተመለከተ በክልል እና ከተማ አስተዳደሮች ተፈፃሚ እንዲሆን የሚደነግግ ነው።

የተሻሻለው አዋጅ የወሰን ማስከበር ሥራ፣ ንብረት የማስነሳት ስራዎችን ለማከናወን ይፈጠር የነበረውን አላስፈላጊ ጫና እንደሚያቀልም ተመላክቷል፡፡

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤  አዋጁ ከጸናበት ቀን በፊት ውሳኔ ያገኙና ክፍያ በመጠባበቅ ላይ ያሉት ጉዳያቸው ከአሁን በፊት በነበረው አዋጅ እንዲፈጸምላቸው እንደሚጠቅስ ገልጸው ‘ውሳኔ ያገኙ’ የሚለው ቀርቶ ከአሁን በፊት የተጀመሩ ፕሮክጅቶችና ካሳ ያልተከፈላቸው በነባሩ አዋጅ ፍጻሜ እንዲያገኙ ተብሎ ቢስተካከል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ከዚህ በፊት በክልሎች ያሉ የልማት ተነሺዎች ካሳ እንዳልተከፈላቸው ጠቅሰው፤ ጉዳዩም በአዲሱ አዋጅ በግልጽ መካተት እንደነበረበት ጠቁመዋል፡፡

ተነሺዎች ቀድመው የመሰረቱት ማህበራዊ ህይወት ላይ ሲነሱ ከፍተኛ የሆነ የሥነ ልቦና ጉዳት ሊያስከትልባቸው እንደሚችልም በመግለጽ ከዚህ አንጻር አዋጁ በግልጽ ስነልቦናቸው እንዳይጎዳ ምን ይደረጋል? የሚለው በግልጽ ቢቀመጥ አዋጁን የበለጠ ጠንካራ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

እንዲሁም የካሳውን የገንዘብ ምንጭ በሚመለከት የፌደራል መንግስት ከሚደጉመው በጀትና ክልሎች ከሚያገኙት የውስጥ ገቢ እንደሚሸፈን በአዋጁ መገለጹን በማንሳት ክልሎች ወቅቱን ያገናዘበና ለካሳ ክፍያ የሚሆን ገቢ እያመነጩ ስለመሆናቸው ተጠይቋል።

የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ÷ ማንኛውም ከዚህ በፊት ከካሳ ክፍያ ጋር የሚያያዙ ጉዳዮች በነባሩ አዋጅ ፍጻሜ እንደሚያገኙ መደንገጉን ተናግረዋል፡፡

ከልካይ የአሰራር ስርዓት በአዲሱ አዋጅ የተደነገገ የለም የተባለም ሲሆን÷ በተገቢው መንገድ በቂ ካሳ አላገኘሁም የሚል አካል በየደረጃው ካለው ፍርድ ቤት በተጨማሪ እስከ ፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ መከራከርና ፍትህ ማግኘት ይችላል ተብሏል፡፡

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button