ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ የሰላም ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ በህግ ቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ 

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 2/ 2016 ዓ/ም፦  የሰላም ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ በህግ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፀጥታና ደኀንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል።

ሚንስትር ደኤታው በማህበራው ትስስር ገጻቸው በተደጋጋሚ መንግስትን ሲተቹ የሚስተዋሉ ሲሆን በቅርቡ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ “በመንግስት እና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መካከል የተካሄደው የሰላም ድርድር ላለመሳካቱ ምክንያት መንግስት ነው” በማለት መናገራቸው ይታወሳል። ይህንን ተከትሎ ጠ/ሚ አብይ አህመድ ከታህሳስ 1 ጀምሮ አቶ ታዬን ከሃላፊነታቸው አንስተዋል።

ግብረሃይሉ ዛሬ ባወጣው መግለጫው “በመንግስት ቁጥጥር ስር ሊዉሉ እንደሚችል ሲገምት ታጋይ ለመምሰል በራሳቸውና በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾች አፍራሽና ፀረ ሰላም ፅሁፎችን፣ ንግግሮችንና መግላጫዎችን በማን አለብኝነት ሲያስተላልፉና ሲሰጡ በመቆየታቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል” በሏል።

ግብረ ኃይል “ታዬ ደንደአ ከህዝብና ከመንግስት የተሰጣቸውን ሀላፊነት በተለይም ደግሞ የሰላም ሚንስትር ዴኤታ ሆኖ ሰላምን ለማስፈን መሥራት ሲገባቸው፤ በተቃራኒዉ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ ፀረሰላም ኃይሎች ጋር በመተሳሰር  ለጥፋት ተልዕኮ በህቡዕ ሲሰሩ ተደርሶባቸዋል” ሲል አስታውቋል። ግብር ሃይሉ ተለያዩ አካባቢዎች በንፁሃን ዜጎች ላይ ሲፈፀሙ በነበሩ የሽብር ተግባራት በተለይም ደግሞ ከእገታ ጋር በተያያዘ እጃቸው እንደአለበት ተደረሶባቸዋል ነው ያለው። 

ታየ ደንደአ የመንግስት ስልጣን ላይ ሆነው በተደጋጋሚ መንግስትን “ገዳይና ጨፍጫፊ” እያሉ ሲወቀሱ የሚደመጡ መሆናቸውን የጠቀሰው የግብረ ሀይሉ መግለጫ “በተግባር ግን ከሽብርተኞች፣ ጽንፈኛችና ነፍሰ ገዳዮች ጋር የጥፋት ትስስር የነበሩት ራሳቸው መሆኑ” በተደረገ  ክትትል  መረጋገጡን ጠቁሟል።

ታየ ደንደአ መንግስታዊና የፓርቲ መዋቅሩን “በሴራ ለመናድ” በህቡእ  እንቅስቃሴ ሲያደረጉ መቆየቸውን በመረዳት  ያላሰለሰ ጥናትና  ክትትል ሲደረግባቸው ነበር ያለው የግብርህይሉ መግለጫ በክትትሉም መንግስት “ሸኔ” ሲል ከሚጠራው ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮችና በሽብር ወንጀል ከተጠረጠሩ ጽንፈኛ ኃይሎች ጋር ትስስር በመፍጠር መንግስትን በአመጽ፣ በሽብርና፣ በትጥቅ ትግል ለመጣል ሲያሴሩ ተደረሶባቸዋል ብሏል። 

በህግ ቁጥጥር ሥር በዋለበት ወቅትም በመኖሪያ ቤቱ ዉስጥ በተደረገ ፍተሻ፤ “ግለሰቡ በህቡዕ ለሚያደርገዉ  ፀረ-ሰላም  እንቅስቃሴ ሲገለገልባቸዉ የነበሩ  የተለያዩ 9 ሞባይሎች፣ 4 ላፕቶፖች፣ 3 አይፖዶች፣ በርካታ ፍላሾች፣ 4 የተለያዩ ተሸከርካሪ  ሰሌዳዎች እና ልዩ ልዩ  የኤሌክትሮኒክስ  መሳሪያዎች፣ ክላሽንኮቭ ጠመንጃና  ሽጉጦች ከመሰል ጥይቶች ጋር እንዲሁም  የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አርማዎችና በተለያዩ ግለሰቦች ስም የተዘጋጁ የቡድኑ መታወቂያዎች፣ ሰነዶችና ማስታወሻዎች” ተገኘተዋል ተብሏል።  

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ከዚህም ባሻገር በብርበራ ወቅት በመኖሪያ ቤት ውስጥ በሶስት መታወቂያዎች የሚጠቀም አንድ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባል ተደብቆ መገኘቱንና በቁጥጥር ሥር መዋሉንም መግለጫዉ ጨምሮ  ገልጿል።

በመንግስትና በፓርቲ መዋቅር ዉስጥ ሆነዉ በተመሳሳይ እኩይ ዓላማ በተሰማሩ አካላት ላይ በጥናት የተመሰረተ ጥብቅ ክትትል በግብረ ሃይሉ እንደሚገኝና የሚወሰዱ ህጋዊ እርምጃዎችን ለህዝብ ይፋ የሚያደርግ መሆኑን መግለጫዉ አስታዉቋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button