ፖለቲካትንታኔ
በመታየት ላይ ያለ

ጥልቅ ትንታኔ: በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ያለው የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ሙያ፤ የሚታሰሩና ሀገር ለቀው የሚሰደዱ ጋዜጠኞች ቁጥር ማሻቀቡ ለምን?

በሚሊዮን በየነ @MillionBeyene


አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13 /2016 ዓ.ም፡- ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ጋዜጠኞች ለእስር እና ለእንግልት የሚዳረጉባት አገር መሆኗን አለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሲገልፁ ይሰማል። አለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲፒጄ ከሁለት ወራት በፊት ባወጣው መግለጫ በአሪቱ ላለፉት አራት አመታት በተለይ በፖለቲካ ውጥረት እና ግጭት ወቅት ተደጋጋሚ የጋዜጠኞች እስር ይከናወናል ሲል ገልጿል።

በቅርቡ በአማራ ክልል ከተቀሰቀሰው ግጭት ጋር ተያይዞ በታወጀው የአቸኳይ ጊዜ አውጅ በርካታ ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ትላንት ጥቅምት 12፣ 2016 ባወጣው መግለጫ “በአስቸካይ ጊዜ አዋጅ ውስጥም ቢሆን በጋዜጠኞችና በመገናኛ ብዙሃን ተቀማት ላይ የሚኖር ተጠያቂነት በህጉ አግባብ ብቻ መከናወን ይኖርበታል። ይህ አለመሆኑ ግን ሀገሪቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ያላት ገፅታ ላይ ጥላ የሚያጠላ ሆኗል” ብሏል፡፡

በተደጋጋሚ እንደሚስተዋልው በቁጥጥር ስር የሚውሉ ጋዜጠኛች ለተወሰኑ ወራቶች በእስር ቤት እንዲያሳልፉ ከተደረጉ በኋል በተጠረጠሩበት ወንጀል ሲፈርድባቸው አይስተዋልም። ይህ የሚሆነው ይላሉ በርካቶች የሚታሰሩት ጋዜጠኞች ወንጀለኞች ሆነው ሳይሆን በስራው መንግስት ደስተኛ መሆን ባለመሆኑና ዝም ለማሰኘት ሲሉ ሀሳባቸው ይሰነዝራሉ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በመግለጫው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ጋዜጠኞች ላይ ከሕግ አግባብ ውጪ አስሮ የማቆየት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ገልጦ በመገናኛ ብዙሃን አማካይነት በወንጀል ሥነ-ሥርዓት የሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዓቃቤ ሕግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበት በመገናኛ ብዙኃን አዋጁ በግልጽ ቢደነገግም መንግስት ይህን አእየከወን አይደለም ብሏል።

በጋዜጠኞች እስርን በተመለከተ በተደጋጋሚ መግለጫዎችን የሚያወጣው ሲፒጄ አሁንም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ህዝቡ በተለያዩ ግጭቶች ዙሪያ የተለያዩ ዘገባዎችን እና አስተያየቶችን ማግኘት በሚፈልግበት ጊዜ በጋዜጠኞች ላይ እያነጣጠረ ነው ሲል ወቅሷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተደጋጋሚ በሚደርስባቸው እስር በመማረር እና በእስራቸው ወቅት በቤተሰቦቻቸው ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ ለማስቀረትም በርካታ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ሰዎች አገር ለቀው መሰደዱ ማየት የተለመደ እሆነ መጥቷል። 

የቅርብ ግዜ መንግስታትን ታሪክ ስንመለከት እንኳ በሙያቸው ሳቢያ በመንግስት በሚደርስባቸው ጫና ሀገራቸውን ጥለው መሰደዳቸው የተመለከቱ በአለም አቀፍ የመብት ተቆርቋሪ ተቋማት እና በመገናኛ ብዙሃኑ ዘገባዎች ከማይጠፉ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ነው። አሁንም በኢትዮጵያ የሚሰደዱ ጋዜጠኞች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። “ምንም መስራት አልቻልንም የሚያሰራ ምህዳር የለም” ሲሉ በርካታ ሙያተኞች ይናገራሉ፤ “የመንግስት ጫና ከግዜ ወደ ግዜ በስፋት እየጨመረ ነው” ሲሉ ይገልጻሉ። 

በቅርቡ በሽብርተኝነት ተጠርጥሮ በእስር ላይ የነበረው በኋላ ላይም ከእስር ተለቆ፤ ሀገራቸውን ጥለው ከተሰደዱ እና ለስደታቸው ዋነኛ ምክንያት ደግሞ “የመንግስት ያደረሰብን ጫና ነው” ሲሉ ከተደመጡት መካከል የኢትዮሰላም የዩቱዩብ ሚዲያ መስራች እና የፖለቲካ ተንታኙ ቴዎድሮስ አስፋው ይገኝበታል። ቴዎድሮስ አስፋው ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረገው ቆይታ “ለስደቴ ዋነኛ ምክንያት በሙያየ ምክንያት በተደጋጋሚ ይደርስብኝ የነበረው እስር እና ጫና ነው” ሲል ገልጿል። ከእስሬ ጋር የተያያዙ ዛቻ እና ማስፈራሪያዎች እጅግ አስጨናቂዎች ናቸው ሲል ያስረዳው ቴዎድሮስ ስራየን በነጻነት የምሰራበት ሁኔታ ባለመኖሩ ነው የተሰደድኩት እንጂ እነዚህ ሁኔታዎች ባይኖሩ ለመሰደድ ምንም ምክንያት አይኖረኝም ነበር ሲል ገልጿል።

ሀገሬ ላይ ሁኜ ከቤተሰቤ ጋር፣ በሙያዬ አገለግለዋለሁ ከምለው የማህበረሰብ ክፍል ጋር ሆኜ ስራየን እየሰራሁ መኖር የመጀመሪያ ምርጫየ ነበር በማለት ለአዲስ ስታንዳርድ የተናገረው ቴዎድሮስ ማስፈራሪያና ዛቻዎች በመኖራቸው፣ ከዚህም አልፎ በኔ ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቼም ጋር ስጋት የሚፈጠር እንቅስቃሴዎች ከመንግስት በኩል በመኖራቸው ነው ከሀገር ለመውጣት የተገደድኩት ብሏል።

በቤተስብ ላይ ያላው ጫና

የቴዎድሮስ አስፋው ባለቤት እና የልጁ እናት የሆነችው እናት አለማየሁ በበኩሏ ባለፉት ሁለት አመታት በነበረን የትዳር ዘመን በተደጋጋሚ መታሰሩ የፈጠረብኝ ጫና ከፍተኛ ነው ስትል ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጻ ይህም ይሰማት ከነበረው ጭንቀት ጋር ስታወዳድረው ስደት ይሻል ይሆን? የሚል ሃሳብ እንዳጫረባት ተናግራልች፡፡ በተደጋጋሚ የጸጥታ ሀይሎች እየመጡ ቤታችንን ይፈትሹ ነበር፣ ልጃችንን ወልጄ አራስ እያለሁ ታስሮ ነበር ይህ ሁሉ ጫና ባለቤቴ የሚወደው የጋዜጠኝነትን ሙያ በመተግበሩ ነው ስትል ተናግራለች።

ባለቤቴ ቴዎድሮስ በተደጋጋሚ ለእስር ከመዳረጉ በላይ አሁንም በተጨማሪ በሙያው ምክንያት ለእስር እንደሚዳረግ እያሰብኩ መኖር ስቃይ ነው ያለችን እናት አለማየሁ ለእስሩ ምክንያት ሞያው በመሆኑ እና ፖለቲካዊ በመሆኑ ፍትህ ነጻ ያወጣዋል ብየ እንኳ ተስፋ እንዳላደርግ ሆኛለሁ ብላለች። 

ስደት ተስፋ የሚሰጥ አይደለም፤ ነገ ወይም ከወራት አልያም ከአመት በኋላ እንገናኛለን የሚል ተስፋ ያለበተ አየደለም ስትል የነገረችን ባለቤቱ እናት አለማየሁ አንድ ልጅ ነው የወለድኩት ገና ሁለት አመት አልሞላንም ትዳራችን፤ ምርጫ ሲቀርብልኝ መምረጥ የምችለው ይሄንን ነው ስትል ስደቱን መደገፏን አጋርታናለች።

“ከልጄ እና ከእኔ ጋር እንዲሆን ብየ በመንፈሱ የሞተ ባል ይዤ መቀመጥ ምን ይጠቅመኛል?” ስትል ውሳኔዋን አስረግጣለች።

የመገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች ምን ይላሉ?

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት እና የአሃዱ ሬዲዮ እና ቴሌቭዥን ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አንጋፋው ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ የጋዜጠኞች ስደት እና እስርን በተመለከተ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ “እንደ ማህበር የጋዜጠኞች መሰደድ፣ መታሰር በጣም ያሳስበናል፣ ስራው ላይም ከፍተኛ ተጽእኖ እየፈጠረ ነው” ሲሉ ገልጸው በመገናኛ ብዙሃን ዘንድ ጥሩ ያልሆነ ድባብ ተፈጥሯል ሲሉም ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞችን ለእስር እየዳረገ ያለው ሀገሪቱ ባወጣችው የመገናኛ ብዙሃን ህግን ተከትሎ አለመሆኑን የጠቀሙት የማህበሩ ፕሬዝዳንት የሚታሰሩት ጋዜጠኞች ናቸው፣ የሚታሰሩበት ምክንያት ግን ከሞያቸው ጋር የተያያዘ አይደለም፤ አብዛኛው ግዜ “በሽብር” የሚል ነው የእስራቸው ምክንያት ሲሉ ገልጸዋል። 

“ጋዜጠኞቹ ክስ የሚመሰረትባቸውም በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ነው በሚል ምክንያት በመሆኑ እንደ ማህበር ብዙ እንዳንሯሯጥላቸው አድርጓል” ያሉን ጥበቡ በለጠ “እስራቸው በሙያቸው አይደለም የሚለው ነገር በራሱ ሌላ ችግር ስለፈጠረብን ነው” ብለዋል።

ማህበሩ ብዙም እየተንቀሳቀሰ አለመሆኑን የገለጹልን ፕሬዝዳንቱ ምክንያቱ ደግሞ እንኳን ለሌሎቹ ለሞያተኙቹ እና ለአመራሩ እና ለመስራቹም ምንም ማድረግ አለመቻሉን አስታውቀዋል። የማህበሩ መስራች እና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው በእስር ላይ እንደሚገኝ የገለጹት የማህበሩ ፕሬዝዳንት ድካም ተሰምቶናል ሲሉ ተስፋ በቆረጠ ስሜት መልእከታቸውን አጋርተውናል።

በሀገሪቱ ብዙ ጋዜጦች እና መገናኛ ብዙሃን ከገበያ ውጭ መሆናቸውን ያወሱት ጥበቡ በለጠ አሁን በስራ ላይ ያሉትም ቢሆን በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ሁነው እየሰሩ መሆናቸውን አመላክተዋል። ጋዜጠኞች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውረው ሊዘግቡ የሚችሉበት ሁኔታ ካለመኖሩ ባሻገር ለበርካቶች ባለሞያተኞች የጋዜጠኝነት መታወቂያ መያዝ በራሱ ያስፈራል ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

ሌላኛው ባለፉት ሶስት አስርት አመታት በጋዜጠኝነት ሞያ ያገለገለው አንጋፋ ጋዜጠኛ እሸቱ ገለቱ በበኩሉ ለጋዜጠኞች ግዜው ከባድ ሁኗል፤ ኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት የሚከንበት ሀገር አልሆነም ሲል ገልጾ በስደት የሚገኙትን ጋዜጠኞች ነባሮቹንም አዳዲስ ወጣት ሆነው የተሰደዱትንም በተለያዩ አጋጣሚዎች ከሀገር ውጭ አገኝቻቸዋለሁ፤ የሚታየው ስብራት ያማል ሲል ሀሳቡን ለአሲስ ስታንዳርድ አጋርቷል።

“የሀገሪቱ ሁኔታ ለሚዲያ ተቋማት የሚያሰራ አይደለም፣ መረጃ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው፣ እንደ መብት አይቆጠርም” ሲሉ የነገሩን ደግሞ የመቀለ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሙዩኒኬሽን መምህሩ ማቴዎስ ገብረህይወት ናቸው። በአጠቃላይ ጋዜጠኞች ፕሮፌሽናሊ እንዳይሰሩ የሚያደርግ ሁኔታ ነው ያለው፣ መንግስት በሚዲያው ላይ የሚያሳድረው ጫና በጣም ከባድ ነው ብለዋል።

የሚዲያ ምህዳሩ ፖላራይዝድ ነው፤ ሁሉም የየራሱን ፍላጎት በተለይም የፖለቲካ ፍላጎት ለማራመድ ነው የሚውሉት መምህሩ ነጻ ናቸው ብሎ ማህበረሰቡ አመኔታ የሚጥልባቸው፣ ማህበረሰቡ በተወሰነ ደረጃ የሚተማመንባቸው የግል መገናኛ ብዙሃን እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው ብለዋል። 

የሚዲያውና ሙያተናው ዝንባሌ ጉዳይ

በጋዜጠኝነታቸው፣ በሞያቸው ምክንያት ለስደት የተዳረጉ፤ ሙያቸውን አክብረው የሚሰሩ እንዳሉ ሁሉ ሙያቸውን ለሌላ አላማ የሚያውሉ አሉ የሚሉ ቅሬታዎች ይነሳሉ። ጋዜጠኛው የሙያው ስነምግባር ከሚያዘው ይልቅ ለሚወግንለት የፖለቲካ አላማ ይሁን ለመጣበት ማህበረሰብ ብቻ ጠበቃ በመሆን የስነምግባር ግድፈት ይታይበታል ሲባልም ይሰማል። አለፍ ሲል ደግሞ ጋዜጠኝነት ሞያው በሀገሪቱ አደጋ ላይ ነው፣ ሁሉም ሚዲያ እና ጋዜጠኛ ባለስልጣናት ወይንም ባለሀብቶች ኪስ ውስጥ ገብቷል በሚል ሞያው እራሱ ይታማል።

ስለሙያው የሚቆረቆሩ ደግሞ በሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን የተወረሩት ሙያውን በማያውቁት ሰዎች ስለሆነ ነው ሲሉ ይሞግታሉ። ይህንን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ የሰጡት የመቀለ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሙዩኒኬሽን መምህሩ ማቴዎስ ገብረህይወት በሀገራችን በባለስልጣናት ተጽእኖ ስር ያሉ ሚዲያዎች አሉ፣ በባለሃብቶች ተጽእኖ ስር የወደቁ ሚዲያዎችም አሉ፣ ዋናው ስራቸው ሲመዘን ሞያዊ ነው የሚለውን ማየት ነው፤ ከዚህ አንጻር ሞያቸውን የሚተገብሩ ጋዜጠኞች እጅግ አናሳ ናቸው ብለውናል። በተጨማሪም ሁሉም የሞያው ስነምግባሮች በየመገናኛ ብዙሃኑ ተከብረው ባታገኘውም የጋዜጠኝነት ሞያ ላይ ያሉ መካተት ያለባቸውን ነጥቦች ልታገኝ ትችላለህ፤ ነገር ግን በአጠቃላይ ስትመዝነው ሚዲያው ላይ መታየት ያለበትን ስነምግባር አይገኝም ብለዋል።

መምህሩ የሀገሪቱ መገናኛብዙሃን ሙያውን በማያውቁት ሰዎች ከሚደርስበት ችግር የበለጠ ፕሮፌሽናል በሆኑት የሚደርስበት ይበልጣል ሲሉ ገልጸዋል። በማሳያነትም ከዩኒቨርስቲዎች ተመርቀው የሚወጡ ጋዜጠኞች ሚዲያዎቹ ላይ ሲሄዱ እኛ ባስተማርናቸው መንገድ አይደለም የሚሰሩት እዚያ ሚዲያ ላይ ባለ ፖለቲክዊ ሊሆን ይችላል ሌላ ፍላጎተ ላይ ተቀርጸው በዚያው መንገድ እንዲተገብሩ ነው የሚደረገው ሲሉ ገልጸዋል።

እኛ ያስተማርናቸው የጋዜጠኝነት ትምህርት የተከታተሉ አሉ ነገር ግን ጋዜጠኝነትን ሲተገብሩ አይታይም፤ የፕሮፓጋንዳ ጉዳይ ሲያራግቡ ነው የሚታየው፣ እውቀት የላቸውም ማለት አይቻልም፤ በሆነ የፖለቲካ ቡድን ወይንም ፍላጎት ባለው አካል የተጫኑ ናቸው ብለዋል።

ቴዎድሮስ አስፋው በበኩሉ  የሀገሪቱ ሚዲያ ላይ የሚሰሩ ጋዜጠኞች የራስን አመለካከት ማንጸባረቅ ላይ ያተኮረ መሆናቸውን ጠቁሞ ሌላኛውን አካል መረዳት እንኳን የሚፈልግም አይደለም ሲል ይተቻል።

ሚዛናዊ የሆኑ ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚጥር እና ፍላጎቱም ጭምር ያለው የለውም ማለት ይቻላል ሲል ገልጾ ጋዜጠኛው ለአሰሪው ተቋም እና ከሚደግፈው፣ ከሚያራምደው የፖለቲካ አስተሳሰብ ውጭ ያሉትን አስተሳሰቦችንም ሆነ ምክንያቶች ለማዳመጥ/ለመረዳት እንኳን ፍላጎት የለውም፤ መረጃው እንኳ ቢኖረው ብሏል።

ጽንፈኝነት የሀገሪቱን አየር በተቆጣጠረበት ሁኔታ ሙያውን የሚያውቁ ሚዛናዊነትን ሊጠብቁ የሚሞክሩ ይገፋሉ ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ የገለጸው ቴዎድሮስ ገበያው እራሱ የሚፈልጋቸው አይሆንም ስለሆነም በመዚህ ምክንያት ከሙያው ይገለላሉ ብሏል።

ለእነዚህ ነገሮች በሙሉ ሀላፊነት መውሰድ ያለበት መንግስት መሆኑን የጠቆመን ቴዎድሮስ አስፋው “ጽንፈኝነት በዚህ ደረጃ የፖለቲካው መገለጫ ሲሆን ሁላችንም የህልውና አይነት ትግል ውስጥ የምንገባ ከሆነ፤ በእንደዚህ አይነት ወቅት ላይ ሙያተኛ ሁን ማለት እንደቅንጦት የሚታይ ይመስለኛል፤ ይህንን ማርገብ፣ አቻቻይ የሆነ ሚዛናዊ የሆኑ ዘገባዎችን ለመስራት፣ ትንታኔዎችን ለመስጠት የሚረዳ ይመስለኛል” ሲል አካፍሎናል። ስለዚህ ሁሉም የእኔ ነው የሚለውን አካል ከህልውና ለማትረፍ፣ ከተሸናፊነት ለማትረፍ፤ ጥቅሙን ለማስጠበቅ ፍላጎቱን እንዲሟላለት ለማድረግ ሙያውን ጭምር አላስፈላጊ ቢሆንም ተገቢ ባልሆነ ሙያዊ ባልሆነ መንገድ ለመጠቀም እስከመገደድ ይደርሳል ማለት መሆኑን አመላክቷል።

የሀገሪቱ የጋዜጠኝነት ሞያ ዋነኛ ችግር ሞያው የተሞላው ሞያውን በማያውቁት ሰዎች መሆኑ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት የሆነው ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ለአዲስ ስታንዳርደ አስተያየቱን አጋርቷል።  የእኛ ሀገር የጋዜጠኝነት ሞያ ከመጀመሪያውም ጀምሮ በብዙ ችግሮች ውስጥ ያለና የመጣ ነው ሲል የነገረን ጥበቡ በለጠ በሀገሪቱ ሙያው በባለሞያተኞች የተያዘ እንዳይደለ እና ትኩረት እንዳልተሰጠው ግልጽ ማሳያ ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ ነጻ መገናኛ ብዙሃን እና የኢትዮጵያ የግል ባንኮች በእኩል ዘመን ወደ ስራ መግባታቸውን ያወሳው የማህበሩ ፕሬዝዳንት ነገር ግን ዛሬ ባንኮቹ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ ገንብተው ቢዝነሶችን የሚያንቀሳቅሱ የኢኮነሚው አውታር ሆነዋል፣ መገናኛ ብዙሃኑ ደግሞ ከምድር ላይ የመጥፋት ሁኔታ ነው የሚታይባቸው ሲል በንጽጽር አቅርቧል።

ይህ የአየያዝ ጉዳይ ነው ያለን ጥበቡ ባንኮችን መንግስተ ስለሚደግፋቸው፣ ስለሚቆጣጠራቸው እንዲያድጉ እንዲበለጽጉ ብዙ ነገር ስለሚደረግላቸው አደጉ፤ መገናኛ ብዙሃኑ ስለሚኮረኮሙ እና ብዙ ጫና ስላለባቸው ተዳክመው ሞቱ ማለት ይቻላል ብሎናል።

የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ወደ መዝናኛው ዘርፍ እያተኮሩ ይገኛሉ ለምን?

የህዝብ አጀንዳ የሚያቀነቅኑ የግል መገናኛ ብዙሃን እየከሰሙ ይገኛሉ፣ በአንጻሩ መዝናኛ ላይ የሚያተኩሩ በርካታ የሬድዮ እና የኢንተርኔት ዘርፎች ደግሞ ፈልተዋል፡፡ ይህ ወቅት ወሳኝ የሆኑት ጉዳዮች ለህዝቡ ሊደርሱ የሚገባበት ወቅት ነው። ምሁራንና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ሊከራከሩበት፣ ሀሳብ ሊንሸራሸርበት፣ ውይይቶች ሊደረጉበት የሚሻ ወቅት ነው። ነገር ግን ይህ ሁሉ በሀገሪቱ አይታይም።

በትግራይ ላይ ጦትነት በተካሄደበት ወቅት ሚዲያዎቹ ለምንድን ነው ይሄ ጦርነት የሚካሄደው ከማለት ይልቅ የመንግስት መሳሪያ ነበሩ። የጦርነቱ መሳሪያ ነበሩ። አብዘሃኛዎቹ የመዝናኛ ዘገባዎቻቸውን ትተው ሁሉ ሙሉ አጀንዳቸውን ቅስቀሳ ላይ የጦርነቱ ውሎዎች ላይ ትኩረት ያረጉበት ግዜ ነበር። ሚዲያው የሀገር ውስጥ ጦርነት እንጂ ከውጭ ጠላት ጋር የሚደረግ ጦርነት አለመሆኑን የሚያጠይቅ ፕላትፎርሙን መፍጠር ነበረበት። ግን አላደረገም። 

በሀገር ውስጥ ተመዝግበው ከሚሰራጩ መገናኛ ብዙሃን ችግር ሳይደርስባቸው የነጻነት አየር በመተንፈስ ላይ ያሉት በመዝናኛው ዘርፍ የተሰማሩት ብቻ ይመስላል። በሀገሪቱ በተለይም በዋና ከተማዋ ያሉ የአጭር ስርጭት ሬድዮ ጣቢያዎችም ሆነ፣ ተመዝግበው፣ ፍቃድ አግኝተው በኢንተርኔት የሚተላለፉ መገናኛ ብዙሃኑ ትኩረታቸው መዝናኛው ላይ ከሆነ ሰነባብቷል። ለምን ስንል ጠየቅን፤

የመቀለ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሙዩኒኬሽን መምህሩ ማቴዎስ ገብረሂዎት አስተያየት “ሽሽት ነው” ሲሉ ምላሻቸውን የሰጡን ሲሆን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ጥበቡ በለጠ በበኩሉ አያስጠይቅማ” ብሎናል። መምህር ማቴዎስ ገብረሂዎት የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን መዝናኛ ላይ እንዲያተኩሩ ያደረጋቸው ሽሽት እና ፍራቻ ዋናው ገፊው ምክንያት ነው ሲሉ ገልጸው በመዝናኛው ዘርፍ እራሱ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ከማንሳት ይልቅ የውጭ ሀገራት የመዝናኛ ጉዳዮችን እንደሚያበዙ ተናግረዋል። ፖለቲካ የሚፈራበት አትሞስፌር ስለተፈጠር ወደ መዝናኛው ፊታቸው መዞሩን አመላክተዋል።

ጥበቡ በለጠ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት በበኩላቸው የመዝናኛ ዘገባዎች ስለማያስጠይቁ እና ወደ ፍራቻ ቆፈን ውስጥ ስለማያስገባ ነው ሲሉ ገልጸው ትኩረቱ በአውሮፓ እግር ኳስ እና መዝናኛ ላይ መሆኑ ህዝብን በተለይም ወጣቱን ለማደንዘዝ ብቻ ነው የሚጠቅመው ሲሉ ትዝብታቸውነ አካፍለውናል። ታላላቅ የሀገሪቱ ድርጅቶች እና ተቋማት ገንዘባቸውን አፍስሰው ህዝቡን የሚያደነዝዙ ሁነቶችን ስፖንሰር እንደሚያደርጉ በመግለጽ ተችተዋል።

መታወቅ ያለበት ይላሉ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ መገናኛ ብዙሃኑ በተለይም የሀገራችን ሬድዮና እና ቴሌቪዥኖች መዝናኛ አይደለም የሚቀርበው፤ መዝናኛ ሌላ ዘውግ ነው ሲሉ ገልጸው የኛዎቹ የሚያቀርቡት የመዝናኛ ዘገባ ሳይሆን የማደንዘዣ ዘገባ ነው ሲሉ አሳስበዋል።  መዝናኛ ሙያ ነው፣ ሙያተኛም ይፈልጋል፤ በመዝናኛ ውስጥ ሰውን ማሳወቅ፣ ሰውን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሳደግ፣ አዕምሮአዊ ብቃት እንዲኖረው ማድረግ  ላይ አተኩሮ የሚሰራ ነው። እያዝናናህ የምታስተምርበት ነው እንጂ የምታደነዝዝበት አይደለም። እኛ ጋ ወደ ማደንዘዣነት ነው የተቀየረው ይህ ያሳዝናል ብሏል።

በስደት የሚገኘው ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ አስፋው በበኩሉ አሁን ላይ ሀገር ውስጥ ያለው ሚዲያ እንዴት ነው ፖለቲካ ሊሰራ የሚችለው ሲል በመጠየቅ  ሀገር ውስጥ ያለው ሚዲያ ፖለቲካ መስራት ስለማይችል እና ችግር ስለሚገጥመው ተገዶ ነው ወደ መዝናኛው የገባው ብሎናል። ፖለቲካ ላይ ትኩረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ ሚዲያዎች በሙሉ ከሀገር ውጭ ያሉ ናቸው ሲል ትዝብቱን አካፍሎናል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button