ዜናፖለቲካማህበራዊ ጉዳይ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በኦሮሚያ ክልል ባለው ግጭት 1.3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ተፈናቅለዋል፤ የህይወት መጥፋት፣ የንብረት ውድመት ተባብሶ ቀጥሏል- ሲዲሲቢ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12/ 2015 ዓ ም፦ በኦሮሚያ ክልል ባለው ግጭት እስከ ግንቦት ወር 1.3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች መፈናቀላቸውን ሴንተር ፎር ዴቭሎፕመንት ኤንድ ካፓሲቲ ቢዩልዲንግ (CDCB) አስታወቀ።

ድርጅቱ ከሁለት ባሳለፍነው ሳምንት ባወጣው ሪፖርት በክልሉ እየተካሄደ ያለው ግጭት ካስተለው መፈናቀል በተጨማሪ የህይወት መጥፋት፣ የንብረት ውድመት ሲባባሱ፣ የልማት ስራዎች ተስተጓጉለዋል እንዲሁም የህዝቡ አብሮ የመኖር ባህል ተመናምኗል ብሏል።

በኦሮሚያ ክልል ከተፈናቀሉት 1,292,323 ዜጎች ውስጥ 374,400 (29 በመቶ) የሚሆኑት በቻ መጠለያ ውስጥ መሆናቸውንና የተቀሩት 71 በመቶ ተፈናቃዮች በማህበረሰቡ ውስጥ ተበትነው መኖራቸውን ተቋሙ ገልጿል። በምስራቅ ወለጋ እና ምዕራብ ወለጋ ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው ያለው የተቋሙ ሪፖርት 859,000 (66%) የሚሆኑት ከሁለት ዞኖች ብቻ የተፈናቀሉ ናቸው ሲል አስታውቋል። 

“ባደረኩት ጥናት መሰረት፣ ኦሮሚያ ክልል ግጭቶች ተባብሰው መቀጠላቸውን፣ የዜጎች ህልውና አደጋ ለይ መውደቁን፣ የትምህርት እና ጤና እንዲሁም የመንግት ተቋማት በመውደም ላይ መሆናቸውን ተረድቻለሁ” ብሏል። 

በዚህም በክልሉ 739 ትምህርት ቤቶች ከአገልግሎት ውጪ ሆነዋል ያለው ሪፖርቱ ከ210,000 በላይ ህጻናት ከትምህርት ገበታ ላይ ተፈናቅለዋል ሲል ገልጿል። 1,117 መምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች በግጭች ምክንያት ከስራቸው ውጭ ሆነዋል ነው የተባለው።

በተጨማሪም 208 ጤና ተቋማት ሙሉ በሙሉ ሲወድሙ 788 በከፊል መውደማቸውን ከክልሉ ጤና ቢሮ ያገኘሁት መረጃ አመላክቷል ነው ያለው ሪፖርቱ። 10 አምቡላንሶች ተዘርፈዋል፣ 45 የሚሆኑት ደግሞ ተቃጥለዋል 25 ደግሞ ከአገልግሎት ውጭ ሆነዋል ሲልም አክሎ አስታውቋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ተቋሙ በሪፖርቱ በምዕራብ ኦሮሚያ ወረዳዎች እና መካከለኛው አከባቢዎች በኢትዮጵያ መንግስት እና በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች  መካከል የሚስተዋለው ግጭት፣ እንዲሁም በተለይ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በፋኖ ታጣቂ ቡድን የሚደረሰው ጥቃት ውድመት አድርሷል ብሏል።  የደረሰውም ውድመት  ከክልሉ፣ ከፌደራል መንግሰቱና ከግብ-ሰናይ ተቋማት አስቸኳይና እርዳታ እንደሚያስፈልገው ጠቁሟል።

በክልሉ ግድያ እና ስርአት አልበኝነት መስፋፋቱን ያመላከተው ሪፖርቱ ጥቅምት 2015  በምዕራብ ወለጋ ዞን ሳሲሲጋ ወረዳ በገሎ ቀበሌ በመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርሰቲያን በታጣቂዎች በተፈፀመ ጥቃት የ14 ሰዎች ህይወት ማለፉን ለዚህ ማረጋገጫ ነው ብሏል።

በክልሉ የሚስተዋሉት ግጭቶች በተለይ ሴቶች እና ህጻናትን አደጋ የጣሉ መሆናቸውን በመጥቀስ እናቶቻቸውን እና አባቶቻቸውን በድንገት የሚያጡ ህፃናት ቁጥር እየጨመረ መሆኑንመ አመላክቷል። በተጨማሪም ባለቤቶቻቸው የሞቱባቸው ሴቶች ለዝርፊያ እና ለ አስገድዶ መድፈ እና አካላዊ ጥቃት እየተጋለጡ ነው ብሏል።

ተቋሙ በዩኤስኤይዲ ትብብር ባዘጋጀው ሪፖርት የወደሙ መሰረተ ልማቶቸ እንዲስሩ ለአርሶ አደሮች ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል ሲል ጠቁሞ በተዋጊዎች መካከል በአስቸኳይ ሰላም እንዲወርድ አሳስቧል። ሁሉን አቀፍ ውይይት እንዲካሄድ እና ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች አስቸኳይ እርዳታ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።  

በተመሳሳይ መልኩ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ባተኮረ ሁለተኛ አመታዊ ሪፖርቱ በኢትዮጵያ 80 በመቶ የሚሆነው መፈናቀል ኃይል በተቀላቀለባቸው ግጭቶች ምክንያት የሚከሰት መሆኑን  አስታውቋል። ኢሰመኮ ባሳለፍነው ሳምንት መገባደጃ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ  መፈናቀልን ለመከላከል እና በዘላቂነት መፍትሔ ለመስጠት ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይገባል ሲል አሳስቧል።

ኮሚሽኑ ነዋሪዎችን ከመደበኛ የመኖሪያ ቦታቸው ያፈናቀሉ፣ የሰው ሕይወት ያጠፉ፣ ሀብት ያወደሙ፣ አካላዊ ጉዳት ያደረሱ ቡድኖች እና ግለሰቦች በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ በቂ እርምጃዎች አለመወሰዳቸው፤ ተጠያቂነትን፣ የሕግ በላይነት እና የተፈናቃዮችን ፍትሕ የማግኘት መብት የሚነፍግ ነው ሲል ኮንኗል። 

በተጨማሪም የተፈናቃዮች ምዝገባ እና ሰነድ የማግኘት ሥርዓቱ ላይ አሁንም ክፍተት እንዳለበት ጠቁሞ ለተፈናቃዮች በሚደረገውን ድጋፍ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን አስታውቋል።

በሌላ በኩል ስፋቱ አራት ሜትር በአራት ሜትር በሆነ የመጠለያ ሸራ ውስጥ ከአንድ በላይ ቤተሰቦች በጋራ እንዲኖሩ መደረጉ ሴቶች እና ሕፃናትን ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው ሲል ያሳሰበው ኢሰመኮ ለተፈናቃዮች ከሚደረገው ድጋፍ በተጨማሪ የጥበቃ ተግባራት ላይም ክፍተት መኖሩ የበለጠ ለችግር ተጋላጭ እንዳደረጋቸው አመላክቷል።

መንግሥት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ እስከሚቻለው ባለመዘግየት በቂ ምግብ፣ ውሃ፣ መጠለያ፣ የሕክምና እና የጤና አገልግሎቶች፣ ንጽሕና፣ ትምህርት እና ሌሎች አስፈላጊ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ያካተተ በቂ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቋል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button