ዜናማህበራዊ ጉዳይ

ዜና፡ የአሜሪካ የረድኤት ድርጅት ዩኤስኤድ በቀጣይ ወር በመላ ኢትዮጵያ የምግብ እርዳታ አቅርቦት እንደሚጀምር አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 5/2016 ዓ.ም፡- ዩኤስኤድ ከወራት በፊት አቋርጦት የነበረውን የምግብ እርዳታ አቅርቦት ከቀጣይ ወር ጀምሮ በመላ ኢትዮጵያ እንደሚጀምር ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተጎጂዎች ተብሎ የሚቀርብ እርዳታ ላልታለመለት አላማ እየዋለ መሆኑ በመረጋገጡ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤድ በኢትዮጵያ የሚያካሂደውን የእርዳታ አቅርቦት ማቋረጡ ይታወሳል።

የአሜሪካ የረድኤት ድርጅት ዩኤስ ኤድ በመላ ሀገሪቱ ለአንድ አመት ያክል የእርዳታ ስርጭቱን በማካሄድ ለመሞከር ማቀዱን አስታውቋል ያለው ዘገባው በዚህን የሙከራ ግዜ የምግብ እርዳታውን አቅርቦት እና እደላ ለታሰበለት አላማ እና ለሚገባቸው ተረጂዎች መዳረሱን ክትትል እንደሚያደርግ እና ምርምራ እንደሚያከናውን መግለጹን አመላክቷል።    

የረድኤት ድርጅቱ የምግብ አቅርቦቱን የሚጀምረው ለበርካታ ወራት ከመንግስት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ድርድሮች ከተከናወኑ በኋላ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው የኢትዮጵያ መንግስት እና አጋር አካላት የእርዳታ አቅርቦቱ እና እደላ ጋር በተያያዘ የተቀናጀና እጅግ አስፈላጊ ማሻሻያዎች በመከናወናቸው መሆኑን አስታውቋል።

የተከናወኑት ማሻሻያዎች የሀገሪቱን የምግብ እርዳታ አቅርቦት ዘዴ ከስር መሰረቱ የሚቀይር ነው ሲል የረድኤት ድርጅቱ ገልጿል ያለው ዘገባው ተግባራዊ የሚደረገው ዘዴ የምግብ እርዳታው ክትትል እና ምልከታን በተቀናጀ ሁኔታ መቆጣጠር የሚያስችል መሆኑን አመላክቷል።

የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ተረጂዎችን በመለየቱ ረገድ የረድኤት ድርጅቶች ሀላፊነቱን ወስደው እንዲሰሩ የኢትዮጵያ መንግስት መስማማቱን የጠቆመው ዘገባው በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ እርዳታ የሚከፋፈልባቸውን ቦታዎች ያለምንም ገደብ ዩኤስኤድ እና የረድኤት ድርጅቶቹ እንዲጎበኙ እና ቁጥጥር እንዲያደርጉ መፍቀዱን አስታውቋል።

ዩኤስኤድ ከአሜሪካን መንግስት እና ህዝብ የተለገሰን እርዳታ ለታለመለት አላማ መዋሉን እና ለችግር ለተጋለጡ ሰዎች መድረሱ ማረጋገጥ ቅድሚያ የምንሰጠው ነው ሲል መግለጹን ያስነበበው ሮይተርስ በኢትዮጵያ በርካቶች የምግብ እርዳታ በተጋለጡበት ወቅት አስፈላጊ የሆነ የእርዳታ አቅርቦት ዘዴውን ማሻሻሉ ለተገቢው ሰዎች ተደራሽ ለማድረግ  ያስችላል ብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ከቅርብ ግዜያት ወዲህ ሀገሪቱ በትግራይ ተካሂዶ በነበረው ጦርነት እና ከበርካታ አመታት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የተከሰተው ድርቅ ኢትዮጵያ የምግብ እጥረት ቀውስ ውስጥ እንድትገባ ማድረጉን ዘገባው አትቷል።

የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤድ በኢትዮጵያ አቋርጦት የነበረውን የምግብ እርዳታ አቅርቦት ከአራት ወራት በኋላ እንደሚጀምር ማስታወቁን እና የእርዳታ እህል አቅርቦቱ የሚጀምረው በሀገሪቱ ተጠልለው ለሚገኙ የጎረቤት ሀገራት ስደተኞች ብቻ መሆኑንንም መግለጹን አሶሼትድ ፕሬስ የዜና ወኪልን ዋቢ በማድረግ መስከረም 25 ቀን 2016 ዓ.ም መዘገባችን ይታወሳል።

የረድኤት ተቋሙ የእርዳታ አቅርቦቱን ለማስጀመር ውሳኔ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ተጠልለው ለሚገኙ የጎረቤት ሀገራት ስደተኞች ላይ ለሚካሄደው የእርዳታ ማጓጓዝ፣ ማከማቸት እና ማከፋፈል ዙሪያ ምንም አይነት ተሳትፎ እንደማይኖረው ስምምነት ላት በመደረሱ መሆኑን የዩኤስኤድ ቃል አቀባይ እንደገለጹለት የዜና አውታሩ በዘገባው ማስታወቁም ተካቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button