ዜናፖለቲካ

ዜና፡ የሲዳማ ህዝብ በተደራጀ ሙስና፣ በመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት ለተለያየ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ  መጋለጡን ሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21/ 2015 ዓ.ም፡- የሲዳማ ህዝብ በክልል ከተደራጀበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ በመልካም አስተዳደር እጦት፣ በተደራጀ ሙስና፣ ብልሹ አሰራር፣ በፍትሕ እጦት፣ በህገወጥ እስራትና አፈና፣ የቡድን ሴራ ፖለቲካና ጎሰኝነትን መሠረት ባደረገ ቡድናዊ አስተዳደር ስረዓት በመጋለጡ የተነሳ ለተለያየ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ ወድቋል ሲል ሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ገለፀ።

በሲዳማ ክልል ወቅታዊ ክልላዊ ጉዳይን አስመልክቶ መግለጫ ያወጣው ድርጅቱ የክልሉ አመራር በተከተለው በጎሰኝነትና ቡድናዊና አግይ አስተዳደር ስረዓት ምክንያት የህዝቡ አንድነት፣ አብሮነትና ማህበራዊ ዕሴት እየተሸረሸረ መጥቷል ሲል ገልፆ  ህዝቡ እጅግ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ፤ በከፋና ከሀገሪቱ ችግር አንፃር እንኳን ቢታይ እጅግ በጣም በባሰ ሁኔታ ለድህነት፣ ለረሀብ፣ ለጎዳና ተዳዳሪነትና ለልመና ተዳርጓል ብሏል፡፡

ያለውድድር፣ በሙስናና በአድሎዊ አሰራር የሚፈፀም የስራ ቅጥር አቅም ያላቸው ተወዳዳሪዎችን ለስራ አጥነት ቀውስ ከመዳረጉም አልፎ የክልሉ ህዝብ እውቀት ባለቸው ባለሙያዎች እንዳይገለገል አድርጓል ሲልም ከሷል።

የክልሉ መንግስት የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ ሰላማዊ ዜጎችን በተለይ ብልሹ አሰራርን በሚታገሉ ወጣቶችና የፓርቲ አመራሮችን ለማፈን፣ ለመግደልና ለማሰር ሌላ ሴራ እያሴረ መሆኑን የጠቀሰው ፓርቲው በህዝቡ ላይ እየፈጸመ ያለውን በደልና ከፋፋይ አጀንዳውን በንፁሀን ዜጎች ላይ ለመጫን “ሕግ አስከብራለሁ” በሚል ሰበብ ህግን በማፍረስ የለመደውን ሽብር ለመፈፀም በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች እየወጡ ነው ብሏል።

በመሆኑም ሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ ፌደራል መንግስት በህጉ በተሰጠው ሀላፊነትና ስልጣን መሠረት በሲዳማ ክልል የተረገውን የሽብር እንቅቃሴ ባቀረብነው ማስረጃ በተደገፈ ጥቆማ መሠረት በአስቸኳይ ምርመራ አድርጎ ፈፄሚዎቹን በህግ ፊት እንዲያቀርብና አሁንም ህግ በማስከበር ስም ሰላማዊ ዜጎችን ለማሸበርና የክልሉን ሰላም ለማናጋት የሚያደርገው እንቅስቃሴ በገለልተኛ አካል አጣርቶ ተገቢ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርቧል።

በተጨማሪም መላው ኢትዮጵያ ህዝብ በሲዳማ ክልል የተሞከረውና በፓርቲያችን ትግል የከሸፈው የሽብር እንቅስቃሴ በሀገሪቱ ዜጎች ላይ በተለያዩ ቦታዎች ከሚደርሱ የሽብር ጥቃቶች ጋር የመገናኘት እድሉ ሰፊ ስለሆን በሲዳማ ክልል በክልሉ መንግስት የተደረገው የሽብር እንቅቃሴና ሙከራ ተገቢ ምርመራ ተደርጎ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ የበኩላችሁን አስተዋፅኦ እንድታደርጉ ሲል ጥሪ አቅቧል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በሰላም ረገድ ህዝቡና ወጣቱ ይህ ሁሉ በደልና ችግር እየደረሰበት ቢሆንም በከፍተኛ ትዕግስት ሰላማዊ ትግል ብቻ እያደረገ በመሆኑ የክልሉ ሰላም ተጠብቆ ቆይቷል ያለው ፓርቲው የክልሉ መንግስት ግን ሀሳባቸውን የሚገልፁትን ወጣቶች ለማፈን፣ ለማሰቃየትና ለመግደል የተለያዩ መዋቅራዊ ሰራዎችን ስሸርብና ስተገብር መቆየቱ ገልጧል።

ለአብነት ያህል ከአንድ አመት በፊት የክልሉ መንግስት በፀጥታና ደህንነት ቢሮዎች አማካይነት በጫንጌ ካምፕ የነበረውን የክልሉን ልዩ ሀይል አባላትን በመጠቀም “የሲዳማ ነፃነት ሠራዊት/ሲነሠ” የተሰኘ ኢ-መደበኛ የሽብር ሀይል በመፍጠር እንዲሁም በሚዲያ በክልሉ የፀጥታ ቢሮ አማካይነት በይፋ “እየገደልን እናስተካክላለን” የሚል መልዕክት ሲያስተላልፉ ነበረ ሲል ገልጧል።  መግለጫው ይህንን ኢ-መደበኛ የሽብር ሀይል የተደራጀበት ዋና ዓላማ በዚህ ቡድን አማካይነት በክልሉ ህዝብ ላይ የተለያዩ የሽብር ወንጀሎችን በመፈፀም ጉዳዩን ከፓርቲያችን ጋር በማገናኘት በፓርቲውና በፓርቲ አመራሮች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን ለመውሰድና ማንኛውንም የክልሉን ሙስናና ብልሹ አሰራር በሚያጋልጠው ሀይል ላይ እስራት፣ ግድያና የተለያዩ እርምጃዎች ለመፈፀም እንደሆነ ፓርቲያው በተጨባጭ ማስረጃዎች አረጋግጧልም ነው ያለው።

ፓርቲው ይህንን መዋቅራዊ የሽብር እንቅስቃሴን በተመለከተ ድርጅቱ ለፌደራል አቃቤ ህግና ለፌደራል ፖሊስ ኦፍሰላዊ የወንጀል ጥቆማ ከነሙሉ ተጨባጭ ማስረጃ ጋር በማያያዝ ያቀረበ ቢሆንም እስከአሁን በህግ ፊት የቀረበ ነገር አላየንም ብሏል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button