ዜናፖለቲካ

ዜና፡ ኢዜማ ሊቀመንበሩ ዶ/ር ጫኔ ከበደ በጸጥታ አካላት በቁጥጥር ሥር የዋሉት ከፓርቲው ጋር በሚገናኝ ጉዳይ አይደለም ሲል ገለፀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21/ 2016 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደ በጸጥታ አካላት በቁጥጥር ሥር የዋሉት በፓርቲው ባላቸው ኃላፊነት ሳይሆን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሠረት በኮማንድ ፖስቱ በመጠርጠራቸው ነው ሲል ፓርቲው አስታወቀ፡፡

ሊቀመንበሩ መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም በጸጥታ አካላት በቁጥጥር ሥር መዋልን ተከትሎ በማግስቱ ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ይህን መሰል ህግ እና ሥርዓት ያልተከተለ እርምጃም በፅኑ እንደሚያወግዘው ገልፆ ነበር፡፡

ድርጅቱ በዛሬው መግለጫው የኢዜማ ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የእስራቸውን ጉዳይ እንዲከታተል የሰየመው ኮሚቴ ባደረገው ማጣራት ዶ/ር ጫኔ ከበደ የታሰሩበት ምክንያት ከፓርቲው ጋር በሚገናኝ ጉዳይ አለመሆኑን መረጃዎች አግኝተናል ሲል ገልጧል፡፡

ኢዜማ ይህንን ይፋ ባደረገበት መግለጫው “ድርጅቱ ውስጥ የማይነካም ሆነ የማይተካ አባልም ሆነ አመራር የለም! ስለሆነም ከድርጅቱ ዓላማ እና የትግል መስመር ባፈነገጠ መንገድ በሚንቀሳቀሱ አባላቱ ላይ የፀና አቋም ይይዛል” ብሏል።

“የኢዜማ አባላት ከሰላማዊ ትግል እና ከዜግነት ፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውጭ ያለን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ መደገፍ፣ የሀሳብም ሆነ የተግባር ተሳትፎም ሆነ ትብብር ማድረግ ከኢዜማዊነት መርኅ ማፈንገጥ” መሆኑን ያስገነዘበው ፓርቲው፣ የሊቀመንበሩ ጉዳይም ከዚህ  መርኅ አንጻር የሚታይ ይሆናል ሲል ገልጧል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሃገራችንን ሰቅዞ የያዘው የፖለቲካ ውጥረት መነሻ በአንድ በኩል በእውቀት፣ እውነት፣ መርኅ እና ምክንያታዊነት ምሶሶዎች ላይ የተመሠረተው የዜግነት ፓለቲካ እና ተበደልኩ፣ ተገለልኩ፣ የሚገባኝን ያህል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እና የፖለቲካ ውክልና ተነፍጎኛል . . . ባህሌን፣ ቋንቋዬን እና ወግ ሥርዓቴን ማሳደግ አልቻልኩም በሚሉ በዘውግ ላይ በተንጠለጠለ ልዩነትን መሰረት ባደረገ የማንነት ፖለቲካ መካከል ሲደረግ የቆየው ግብግብ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ ነው ብለን እናምናለን ብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ኢዜማ ከሰላማዊ የትግል ስልት ውጪ በዘውጌ ብሔርተኝነትም ሆነ አፈሙዝ በታከለበት የትግል መንግሥታዊ ሥልጣን ለመያዝ መንቀሳቀስን ድርጅቱ የማይሳተፍ እና የቆመበትን መርኅ መቃረን አድርጎ ያየዋል ሲል ጠቅሶ ማንኛውም የኢዜማ አባል እና አመራር ከዚህ ፅኑ ዕምነት ውጭ የተንቀሳቀሰ እንደሆነ ድርጅቱን ለማፍረስ እንደሚሰራ ተደርጎ እንደሚቆጠር መታወቅ አለበት ሲል አሳስቧል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button