ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ አሁንም በማንነታቸው ምክንያት የታሰሩ በርካታ የትግራይ ተወላጅ የመከላከያ አባላት እንደሚገኙ አቶ ጌታቸው ረዳ አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19/2016 .ም፡ በፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት በርካታ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የመከላከያ አባላት ክሳቸው እንዲዘጋ በማድረግ የተፈቱ ቢሆንም አሁንም በማንነታቸው ምክንያት የታሰሩ በርካታ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የመከላከያ አባላት እንደሚገኙ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ገለፁ።

ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ ከህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጋር በመሆን ትላንት መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም በጋራ በሰጡት መግለጫ ነው ይህንን ያስታወቁት።

አሁንም በአማራ ክልል ሁነ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ታስረው የሚገኙ በሽዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ይገኛሉ ያሉት አቶ ጌታቸው ከፌደራል መንግስቱ ጋር ባለን ግንኙነት መሰረት እንዲፈቱ ጥረት እያደረግ እንገኛለን ብለዋል።

በፌደራል መንግስቱ በኩል የሚነሱ ጉዳዮች አሉ ሲሉ የተደመጡት አቶ ጌታቸው እኛ ልንፈጽማቸው የሚገቡ፤ ለምሳሌ ያክል በእጃችን ከሚገኙ በምርኮ የያዝናቸው ጋር በተያያዘ ከፌደራል መንግስቱ በኩል ከሚነሱት ውስጥ ይጠቀሳል ሲሉ ጠቁመዋል።

አቶ ጌታቸው በተጨማሪም በተለይ ግን በአማራ ክልል በእስር የሚገኙ የትግራይ ተወላጅ የመካላከያ ሰራዊቱ መኮንኖች ያሉበት ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ ነው ሲሉ ገልጸዋል።  

ከመርዶ ጋር በተያያዘ የሰማዕታቱን ክብር በሚመጥን መልኩ እንደሚከናወን እና በቀጣይ ሳምንት ብሔራዊ ሀዘን እንደሚታወጅ የገለጹት አቶ ጌታቸው በርካታ ቁጥር ያለው ሰማዕታት አሉን፣ እያንዳንዱን ሰማዕት የየት አከባቢ ተወላጅ መሆኑን እና የት እንደተሰዋ የማጣራት እና የመመዝገብ ስራ ባሳለፍነው አመት ሰኔ ወር ነው የተጠናቀቀው ብለዋል። የሰማዕታቱ የትውልድ ቦታ እና የተሰዉበት አከባቢ ልየታ ባሳለፍነው አመት ሰኔ ወር ተጠናቆ ወደ መርዶ ያልተገባው የክረምት ስራዎችን እንዳያስተጓጉል በሚል መሆኑን አስታውቀዋል።

የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል በበኩላቸው ፓርቲው ባካሄደው ስብሰባ የፓርቲው ሁሉም ነገር እንዲፈተሽ ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቀው ከምንከተለው መስመር ጀምረን እስከ ፕሮግራም፣ እስትራቴጂ፣ ስልት ድረስ ይፈተሻል ብለዋል። የምናስተካክለው በርካታ ነገር ይሆናል ሲሉ የተደመጡት ዶ/ር ደብረጺዮን የፓርቲውን ህገ ደንብንም የማስተካከል ስራ እንደሚኖር ጠቁመዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ፓርቲው ሊቀይረው የማይችለው ህዝባዊ ባህሪው ብቻ ይሆናል ያሉት ሊቀመንበሩ ህዝባዊ ባህሪውን ይዞ ሁሉም ነገር ይፈተሽ የሚል ውሳኔ ነው ማዕከላዊ ኮሚቴው ተሰብስቦ ውሳኔ ያሳለፈው ሲሉ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ሊቀመንበሩ በርካታ ችግሮች አሉ፣ ሰላም ከማስከበር ጀምሮ እስከ ሙስና ሲሉ አስታውቀው  ወደ ተጠያቂነት እንደሚሸጋገር አመላክተዋል።

ችግር አለ በሚል ብቻ የሚተው አይደለም፤ ችግር መኖሩ አንድ ነገር ሁኖ ተጠያቂነት ደግሞ መኖር አለበት ሲሉ የተደመጡት ዶ/ር ደብረጺዮን ይህም የሚጀምረው ከታች ሳይሆን ከላይኛው የአስፈጻሚ አካል ነው ብለዋል። ተጠያቂነት ብቻ ሳይሆን እርምጃም እንደሚወሰድ የጠቆሙት የህወሓት ሊቀመንበሩ ፓርቲው ፖለቲካዊ እርምጃ እንደሚወስድ እና ጊዜያዊ አስተዳደሩ ደግሞ የተሰጠውን ስልጣን ተጠቅሞ ሌሎች እርምጃዎችን እንደሚወስድ አስታውቀዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button