ዜናፖለቲካ

ዜና፡ በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ንጹሐን ዜጎች በግፍ እየተገደሉ ነው ሲሉ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮነኑ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 24/2015 ዓ.ም፡- ሀገሪቱን እያስተዳደረ የሚገኘው ገዢው ፓርቲ በአማራ ክልል እያካሄደ ባለው ጦርነት ንጹሐን ዜጎች በግፍ እየተገደሉ ነው ሲሉ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮነኑ።

በኃይል እርምጃ የሕዝብን ጥያቄ መፍታት አይቻልም በሚል ርዕስ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ማለትም ኢሕአፓ፣ መኢአድ፣ ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ፣ አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና እናት ፓርቲ ባወጡት መግለጫ ነው ሁኔታውን የኮነኑት።

ብልጽግና መራሹ መንግሥት የሕዝብን ብሶት ከማድመጥ እና ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ከመፍታት ይልቅ በሚወስደው የሃይል አማራጭ ሕዝቡን ወደ ከፋ ቀውስ ውስጥ እየከተታት ይገኛል ሲሉ ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ተችተዋል።

ከነሐሴ 19 እስከ 22 ቀን 2015 ዓ.ም ባሉት ቀናት ብቻ የመከላከያ ሠራዊት በደቡብ ጎንደር ዞን የእብናት ከተማ በተከታታይ በሰነዘረው የከባድ መሳሪያ ጥቃት ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ህጻናት፣ አረጋውያን እና ሴቶች ያሉበት ንጹሃን መገደላቸውን ከምንጮቻችን አረጋግጠናል ብለዋል።

በተመሳሳይ ደብረ ታቦር፣ በአዲስ ዘመን፣ በወረታ፣ በደብረ ማርቆስ፣ በፍኖተ ሰላም፣ በላሊበላ እና በሌሎቹ የክልሉ አካባቢዎች ላይም ጥቃቱ ተጠናክሮ በመቀጠሉ ንጹሐን ዜጎች በከፍተኛ ስጋት እና መከራ ውስጥ ይገኛሉ ሲሉ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ዋና ዋና መንገዶች በጦርነቱ ሳቢያ በመዘጋታቸው ለእለት ጉርስ እና ጤና አስፈላጊ የሆኑ ሸቀጦችና የፍጆታ እቃዎች ለህዝባችን እንዳይደርሱ ሆነዋል ያለው የፓርቲዎቹ መግለጫ በዚህ ምክንያት ጤፍን ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን አስታውቋል።

በአማራ ክልል የተነሳውን ሕዝባዊ አመጽም ሆነ በደቡብ ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የተነሱ ሕዝባዊ ጥያቄዎችን የኅይል አማራጭ ተጠቅሞ ለመፍታት እየተደረገ ያለው ሙከራ አገርን ወደ ከፋ ቀውስ የሚከት ነው ሲሉ አሳስበዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው በመፍትሔነት ካቀረቡት ሀሳብ መካከል መንግሥት በአማራ ክልል ያሰማራውን የመከላከያ ሰራዊት በአስቸኳይ አስወጥቶ የአገራችን ዳር ድንበር ሊጠብቅ ወደሚችልበት መደበኛ ሥራው እንዲመልስ የሚለው ይገኝበታል።

መንግሥት በክልል ምስረታ ሥም እያከናወነ የሚገኘው የክላስተር ጥርነፋ በቂ ጥናቶች ያልተደረጉበት፣ የተነሱ መሠረታዊ የማህበረሰብ ጥያቄዎችን እና ውሳኔዎችን ያላገናዘበ በመሆኑ በሕገ መንግሥት ማሻሻያ ተገቢው ማስተካከያ እስኪደረግ በጊዜያዊነት ጉዳዩ በድጋሚ እንዲታይ ሲሉ አሳስበዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button