ዜናማህበራዊ ጉዳይ

ዜና፡ በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ በጎርፍ ሳቢያ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥረ 130 ደረሰ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 10/2016 ዓ.ም፡- በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ ከቅርብ ግዜያት ወዲህ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥረ 130 እንደሚጠጋ ተገለጸ።

በቀጠናው የሚንቀሳቀሱ የረድኤት ድርጅቶች ከአንድ መቶ አመት ወዲህ በቀጠናው ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ ጎርፍ መከሰቱን ገልጸዋል ሲል አሶሼትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

በኢትዮጵያ በጎርፍ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሰላሳ መድረሱን ዘገባው አስታውቋል። በጋምቤላ፣ አፋር እና ሶማሊያ ክልሎች የጎርፍ አደጋ መከሰቱን ያስታወቀው ዘገባው በአከባቢዎቹ የተከሰተውን ጎርፍ በመሸሽ ለማምለጥ የሞከሩ ህጻናት ጭምር ሰለባ መሆናቸውን ጠቁሟል።

በሶማሊያ ብቻ ከጥቅምት ወር ጀምሮ በጎርፍ ሳቢያ 51 ሰዎች መሞታቸውን እና ከግማሽ ሚሊየን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የዜና ወኪሉ የሶማሊያ ብሔራዊ አደጋ ማኔጅመንት ኤጀንሲን ዋቢ በማድረግ አስታውቋል።

የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይ ሊጨምር እንደሚችል የአደጋ ሰራተኞች መናገራቸውን ጠቁሟል። ጎርፉ ባስከተለው ውድመት ሳቢያ የሀገሪቱ መንገዶች እና ድልድዮች የመጓጓዣ አገልግሎት መስጠት እንደማይችሉ ዘገባው አመላክቷል።

ጎርፉ አደጋ ላይ የጣላቸውን ዜጎቹን ለመታደግ የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ሄሊኮፕተሮችን እና ጀልባዎችን ማሰማራቱን የሶማሊያ ብሔራዊ አደጋ ማኔጅመንት ኤጀንሲ መግለጹን አስታውቋል።

በኬንያ ከ50 በላይ ሰዎች መሞታቸውን እና ከ30ሺ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የሀገሪቱ የቀይ መስቀል ማህበር ማስታወቁን ዘገባው አካቷል። በኬንያ በባህር ዳርቻ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶች መውደማቸውንም አመላክቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button