ዜናፖለቲካማህበራዊ ጉዳይህግ እና ፍትህ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በአዲስ አበባ ኮማንድ ፖስቱ ያላሳወቃቸው በርካታ እስር ቤቶች መኖራቸውን፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መቀጠላቸውን ኢሰመኮ  አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5/2016 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል በቀጠለው የትጥቅ ግጭት በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ሲቪል ሰዎች ከሕግ/ፍርድ ውጭ በተፈጸሙ ግድያዎች መሞታቸውን፣ ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን እና ንብረታቸው መውደሙን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ትላንት መስከረም 4፣ 2016 ባወጣው መግለጫ የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ኮማንድ ፖስት ካሳወቃቸው እስሮችና ቦታዎች በተጨማሪ በአማራ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የተስፋፋና የዘፈቀደ እስር ተፈፅሟል ሲልም አስታውቋል፡፡

በክልሉ የሰብዓዊ መብቶች ጠሰቶች አሳሳቢነት መቀጠሉን የጠቀሰው ኢሰመኮ በተለይም በአማራ ክልል የትጥቅ ግጭቱ ወደ ክልሉ ልዩ ልዩ ወረዳዎች መስፋፋቱን፣ በነዋሪዎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳትም ተባብሶ መቀጠሉን  ገልጿል። ከነሐሴ 19 እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ በተለይም በደብረማርቆስ ከተማ፣ አዴት፣ መራዊ፣ ደብረታቦር፣ ደልጊ፣ ማጀቴ፣ ሸዋ ሮቢት እና አንጾኪያ ከተሞች እና በአካባቢዎቻቸው በሚገኙ አንዳንድ የገጠር ቀበሌዎች በግጭቱ ዐውድ በርካታ ሲቪል ሰዎች መሞታቸውን፣ ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን እና የንብረት ውድመት ደርሶባቸዋል ብሏል፡፡

በተኩስ ልውውጦች ወይም በከባድ መሣሪያ ተኩስ ከሚሞቱ ሰዎች መካከል በመንገድና በእርሻ ሥራ ላይ እንዲሁም በቤታቸው ውስጥ የነበሩ ሰዎች ጭምር የሚገኙ መሆኑን ቤተሰቦች እና የዐይን ምስክሮች ለመረዳት ችያለው ሲል ገልጧል ኮሚሽኑ።

በተጨማሪም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በመንግሥት የጸጥታ አካላት ከሕግ/ፍርድ ውጭ የተፈጸሙ ግድያዎች (extrajudicial killings) እጅግ አሳሳቢ መሆናቸውን አመላክቷል።

ከሐምሌ 24 እስከ ጳጉሜ 4 ቀን 2015 ዓ.ም በአዴት፣ ደብረማረቆስ፣ በደብረ ታቦር፣ ጅጋ፣ ለሚ፣ ማጀቴ፣ መራዊ፣ መርጦ ለማርያምና ሸዋ ሮቢት ከተሞች፤ ቤት ለቤት በተደረገ ፍተሻ የተያዙ ሰዎች፣ በግጭቱ ወቅት መንገድ ላይ የተገኙ እና ያልታጠቁ ሰዎች፣ “የጦር መሣሪያ ደብቃችኋል አምጡ” በሚል የተያዙ ሰዎች፣ የሰዓት እላፊ ገደቦችን ተላልፈው የተገኙ ሲቪል ሰዎችና በቁጥጥር ስር የዋሉ የፋኖ ታጣቂ ቡድን አባላት ላይ ከሕግ/ፍርድ ውጪ የሆነ ግድያ ተፈፅሟል ብሏል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ከዚህ በተጨማሪም የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ኮማንድ ፖስት በይፋ ካሳወቃቸው እስሮችና ቦታዎች ውጪ በተለይ በአማራ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በአስቸኳይ ጊዜ ዐውዱ የተስፋፋና የዘፈቀደ እስር የተፈጸመ መሆኑን አሰመኮ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ለአብነትም በአማራ ክልል በባሕር ዳር፣ ደብረ ታቦር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ጎንደር፣ ላሊበላ፣ መካነሰላም፣ ቆቦ እና ሸዋ ሮቢት ከተሞች፤ በኦሮሚያ ክልል በተለይ በሸገር ከተማ እና በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጸሙ የዘፈቀደ እስሮች ይገኙበታል ብሏል፡፡ በመንግሥት የጸጥታ አካላት የሚታሰሩ ሰዎች በአብዛኛው “ለታጣቂ ቡድኑ ድጋፍ ታደርጋላችሁ” እና/ወይም “የጦር መሣሪያ ደብቃችኋል” በሚል ምክንያት መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጧል፡፡

በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን፣ ከሕግ/ፍርድ ውጭ የሆኑ ግድያዎችን እና የዘፈቀደ እስሮችን በአፋጣኝ ማስቆም ይገባል ያለው ኮሚሽኑ በየትኛውም ወገን የሚወሰዱ እርምጃዎች ሲቪል ሰዎችን ወይም የመሠረተ ልማቶችን ዒላማ ከማድረግ ሙሉ በሙሉ እንዲቆጠቡ፣ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዳይቋረጥ መከላከል ጨምሮ ለሲቪል ሰዎች ተገቢው ጥበቃ እንዲደረግ፤ በማናቸውም ሁኔታ ሊገደቡ የማይችሉ መብቶችን በተለይም በሕይወት የመኖር መብት እና ከኢ-ሰብአዊ አያያዝ የመጠበቅ መብት እንዲከበሩ አሳስቧል፡፡

አክሎም በሲቨል ሰዎች ላይ ግድያ በፈጸሙና በዘፈቀደ እስራት ላይ በተሳተፉ አካላት ላይ አስፈላጊው ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ፣ ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ትእዛዝ ውጪ የታሰሩ ሰዎች ጉዳይ በመደበኛው የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር መከናወኑ እንዲረጋገጥ፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት የታሰሩ ሰዎችም የተጠረጠሩበት ወንጀል ምርመራ በአስቸኳይ በማጠናቀቅ ፍትሕ የማግኘት መብታቸው እንዲረጋገጥ ጠይቋል፡፡አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button