ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: "ህወሓት መሣሪያ የታጠቀ ኃይል ኖሮት እስከቀጠለ ድረስ እንደ ሀገር ሰላም አይኖረንም” - ኢዜማ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 10/2016 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ – ኢዜማ ዛሬ ሚያዚያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም “መንግሥት ጦርነት የሚጎስመውን የሕወሓት ስብስብ በፕሪቶሪያው ሥምምነት መሠረት ትጥቅ እንዲፈታ በማድረግ ሕግ እና ሥርዓት እንዲያስከብር በአፅንዖት እንጠይቃለን!” የሚል መግለጫ አውጥቷል።

ኢዜማ በመግለጫው “በአላማጣ እና አከባቢው የሕወሓት ታጣቂዎች የኃይል እርምጃ እየወሰዱ እንደሆነ ከተለያዩ የሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን እና ካጣራኋቸው መረጃዎች ለማወቅ ችያለሁ ብሏል።

ሕወሓት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ እውቅና የሌለው “ፓርቲ” ሆኖም መሣሪያ የታጠቁ የራሱ ኃይሎች ያሉት ነው ሲል የገለጸው ኢዜማ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ዛሬም ሽብር እየነዛ የሀገርን ሰላም ማደፍረሱን ቀጥሎበታል ሲል ኮንኗል።

ዛሬም በትግራይ እና በአማራ ክልሎች መካከል ያሉ አወዛጋቢ ቦታዎችን በመሳሪያ አፈሙዝ ያሻኝን አደርጋለሁ በማለት ዳግም ወረራ እየፈፀመ ይገኛል ሲል የገለጸው ኢዜማ በዚህም ሳቢያ ንፁኃን ዜጎች ለአራተኛ ጊዜ ለተጨማሪ እንግልትና ስደት እየተዳረጉ ይገኛል ብሏል።

ሕወሓት “መሣሪያ የታጠቀ ኃይል ኖሮት እስከቀጠለ ድረስ እንደ ሀገር ሰላም አይኖረንም” ያለው ኢዜማ ሕወሓት “ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ያለው ስብስብ ነው” ሲል ገልጿል።

ኢዜማ በመግለጫው “አሁን ክልሎች የተዋቀሩበት አስተሳሰብ እና መንገድ ግጭት ጠማቂ እንደሆነ ብዥታ የለውም ሲል ገልጾ አሁን ላይ እንደ ሀገር ላለንበት ምስቅልቅል መሠረታዊው የቅራኔ ምንጭ ይኸው ሕወሓት ወለድ አስተሳሰብ እና የፓለቲካ አወቃቀር እንደሆነ እንረዳለን ብሏል።

“ጊዜያዊ አስተዳደሩን ሙሉ ለሙሉ “በሆደ ሰፊነት ለሕወሓት ለቀቅኩለት” የሚለው ገዢው ብልጽግና ፓርቲም   ውጤቱ ባለማምጣቱ በአስቸኳይ አማራጭ የማስገደጃ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ ሊገነዘበው ይገባል” ሲል አሳስቧል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

አንዴ “ትጥቅ ፈትተናል” ሌላ ጊዜ ደግሞ “የምን ፈልገውን ለማድረግ በቂ ኃይል አለን” በማለት ከፕሪቶሪያው ሥምምነት ባፈነገጠ መልኩ ሲያምታቱ እየተስተዋለም የፌደራል መንግሥቱ እያሳየ ያለው ኃላፊነቱን በአግባቡ ያለመወጣት፣ ደካማ መረጃ አሰጣጥ፣ ቸልተኝነት እና መሰል ግዴለሽነት የተሞላ ተግባር በእጅጉ የሚያሳዝነን፣ በፅኑ የምናወግዘውም ነው ብሏል፡፡

ትጥቅ የማስፈታቱን ተግባር ውሎ ሳያደር ሊያከናውነው እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተን ለማስገንዘብ እንወዳለን ሲል አሳስቧል፡፡

በመሆኑም የፌደራል መንግሥት ዛሬ ነገ ሳይል አፋጣኝ ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጥ ሲል በመግለጫው የጠየቀው ኢዜማ የፕሪቶሪያውም ሥምምነት ተከብሮ በአስቸኳይ ትጥቅ እንዲፈታ፣ ጦርነት የሚጎስመውን ስብስብም ሥርዓት እንዲያሲዝ እና ሕግ እንዲያስከብር በአፅንኦት እንጠይቃለን ብሏል።

ይህ ሳይሆን ቀርቶ ሕወሓት ሰሞኑን የጀመረው ዳግም ወረራ በዜጎች ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ለሚደርሰው ውድመት እና ምስቅልቅል መንግሥት ሙሉ ኃላፊነቱን የሚወስድ ይሆናል ሲል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኀበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በመግለጫው አስጠንቅቋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button