ዜናፖለቲካህግ እና ፍትህ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በመንግስታቱ ድርጅት የተሰየመው አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ ቡድን ተልዕኮ እንዲራዘም ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 2/2015 ዓ.ም፡- በአለማችን ከፍተኛ ተጽኖ ፈጣሪ የሆኑ ታላላቅ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በጋራ በመሆን የመንግስታቱ ድርጅት በኢትዮጵያ የሚያካሂደውን የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲመረምር ያቋቋመውን ቡድን ተልዕኮን ለተጨማሪ አንድ አመት እንዲያራዝም ጠየቁ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ካውንስል በቀጣይ አመት መጀመሪያ ቀናት 54ኛ ጉባኤውን ያካሂዳል። ጉባኤው ከመካሄዱ በፊት አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂዩማን ራይት ዎች፣ ኦክስፋም እና የአለም የሰላም ፋውንዴሽንን ጨምሮ 63 የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በጋራ በጻፉት ደብዳቤ በኢትዮጵያ በከፋ ሁኔታ እየተፈጸመ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መርማሪ ቡድን በተጨማሪ ለአንድ አመት በማስቀጠል ምርመራ ሊካሄድበት ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ምንም እንኳ የሰላም ስምምነት ቢደረስም አሁንም አስገድዶ መድፈር፣ የሰብአዊ እርዳታ እንዳይደርስ ማድረግ እና የትግራይ ተወላጆችን የማጽዳት ተገባራት በአሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ከቅርብ ወራት ወዲህ የመንግስት ሀይሎች እና ታጣቂ ቡድኖች በአማራ እና ኦሮምያ ክልሎች እየፈጸሙት ያለው ሰብአዊ መብት ጥሰት እጅግ አሳስቦናልም ብለዋል።

በመንግስታቱ ድርጅት የተሰየመው አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ ቡድኑ ተልዕኮ፣ ነጻነት እና ገለልተኛነት በአሁኑ ወቅት ያለገደብ ማስረጃ በማሰባሰብ ተጠያቂነትን ለማስፈን ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ሲሉ የሂዩማን ራይት ዎች የአፍሪካ ዳይሬክተር ሌተሺያ ባደር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የሽግግር ፍትህ ለማካሄድ ቁርጠኛ ነኝ ቢልም በአለም አቀፍ ህግ መሰረት ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ አቅም አለው ብለው እንደማያምኑ ቡድኖቹ በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል። ተጎጂዎች የመንግስት የመሸፋፈን ተግባር ሳይሆን ፍትህ ማግኘት ይገባቸዋል፤በዚህ ሳቢያ የመንግስታቱ ድርጅት የመርማሪ ቡድኑን ሀላፊነት ለተጨማሪ ግዜ በማደስ ሁሉም አካላት የሰብአዊ መብት ጥሰታቸውን እንዲያቆሙ ለሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦ ማድረግ ይገባል ሲሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት ዲፕሮሴ ሙቸና ገልጸዋል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button